አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአርባ ምንጭ ከተማ ቡቡ ሜዳ ለተቋቋመው ለይቶ ማቆያ ማዕከል የቁሳቀስ ድጋፍ አደረገ

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና በሽታን ስጋት ተከትሎ በአርባ ምንጭ ከተማ ለተቋቋመው ለይቶ ማቆያ ማዕከል የአልጋ፣ የፍራሽና የአንሶላ ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርጓል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በተለምዶ ኩልፎ ካምፓስ ተብሎ በሚታወቀው የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የሚገኙ የተማሪ ማደሪያዎችንም ለለይቶ ማቆያ ለማዋል የቅድመ-ዝግጅት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ እንዳሉት የኮሮና በሽታን ለመከላከልና አስከፊ ጉዳት እንዳያደርስ በሚደረገው ጥረት ዩኒቨርሲቲው የበኩሉን ሚና እንደሚወጣና እየተወጣም መሆኑን ገልፀው ለለይቶ ማቆያው የተደረገው ድጋፍም የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት ይህንን ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲውን የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ለለይቶ ማቆያ ማዕከል እንዲሆን የወሰነ ሲሆን ወደ ማዕከሉ ለሚገቡ የቫይረሱ ተጠርጣሪዎች የምግብ አገልግሎትም ጭምር ለመስጠት መወሰኑን ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሁለት ኮሌጆችም የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር እያዘጋጁ መሆናቸውን የጠቆሙት ዶ/ር የቻለ በአሁኑ ሰዓት በምርት ሂደት ውስጥ የተፈጠረውን የአልኮል ዕጥረት ለመቅረፍ ምርቱን ማቅረብ ከሚችሉ ፋብሪካዎች ጋር እየተነጋገርን ነው ብለዋል፡፡

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው በበሽታው ዙሪያ በሚሠሩ ዘርፈ ብዙ የመከላከልና ሌሎች ሥራዎች ወስጥ ዞኑ ዩኒቨርሲቲውን የዐቢይ ኮሚቴ አካል አድርጎ እየሠራ ሲሆን በሽታውን ለመከላከል ብሎም ችግሮች ቢፈጠሩ ለመቅረፍ ከዩኒቨርሲቲው ጋር የጀመርነውን የትብብር ሥራ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡ ይህንንም ድጋፍ ጨምሮ ዩኒቨርሲቲው በሽታው ከተከሰተ ቀን ጀምሮ እየሠራ ያለው ሥራዎች ለሌሎች ተቋማትም አርአያ የሚሆኑና የሚያስመሰግኑ ስለሆነ ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው ናቸው ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ አቶ ሰብስቤ ቡናቤም በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በሽታውን ለመከላከል ላደረገውና እያደረገ ላላው ድጋፍ በከተማው ሕዝብ ስም ምስጋናቸውን አቅርበው ዩኒቨርሲቲው በርካታ የህክምና ባለሙያዎች ያሉት ተቋም እንደመሆኑ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ ይቀጥል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺይፍ ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ የኮሌጃቸው የህክምና ባለሙያዎች በበሽታው ዙሪያ ኅብረተሰቡን ለማንቃትና ግንዛቤ ለመፍጠር ወደ ተለያዩ ወረዳዎች ገጠር ቀበሌያት ጭምር በመሄድ እየሠሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ኮሌጃቸው በሽታው ቢከሰት ህክምና እዚሁ መስጠት እንዲቻል ለህክምና ባለሙያዎች የሚሆኑ የግል መከላከያ ቁሳቁሶችን ከአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጋር በመሆን እያዘጋጀ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ በሽታውን መመርመር የሚያስችል ማሽን በመገኘቱ ከክልል ጤና ቢሮ የመጡ ባለሙያዎችም የታሰበውን አገልግሎት መስጠት እንደሚችል ያረጋገጡ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ታምሩ ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችና ሥልጠናዎች ከሚመለከተው አካል ሲሟሉና ዕውቅናም ከተሰጠን የቫይረሱ ምርመራ እዚሁ ይጀመራል ብለዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት