ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ጽ/ቤት የተላለፈ መልዕክት ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሙሉ

ባሉበት

ውድ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሙሉ፣ ለመላዉ ዓለምም  ሆነ ለሀገራችን ሰው ልጅ ሁሉ በሕይወት ለመኖር እጅግ ከፍተኛ ስጋት ያመጣዉ የኮቭድ-19 መከሰት ምክንያት ለሕዝብና ለሀገር ደህንነት ታስቦ በትኩረት እየተሠራ ካለዉ አንጻር በሀገራችን የሁሉም ትምህርት ደረጃ ተማሪዎች  ወላጅ ወይም ቤተሰብ ዘንድ እንዲቆዩ በተደረገዉ ሂደት ከመጋቢት 19 እስከ 21/2012 ባሉት ቀናት ከዩኒቨርሲቲዉ  ግቢ ወጥታችሁ ወደየቤተሰቦቻችሁ ዘንድ ከሄዳችሁበት ቀን ጀምሮ እንደምን አላችሁ?  ውድ ተማሪዎች የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ  6ቱም ግቢዎች የሚሞቁትና የሚያምሩት እናንተ ስትኖሩበትና በግቢያችሁ ወዲያ ወዲህ (ከዶርም ወደ ክፍል፣ ከክፍል፣ ወደ ላይብራሪና ማጥኛ ቦታዎች፣ ወደ ሻይ/ቡና ወይም መዝናኛ ቦታዎች፣ ወደ አቢያተክርስቲያናትና መስጂዶች ከዚያም ወደ ግቢ፣ ወደ ከተማና ከዚያም ወደ ግቢያችሁ) ሽርጉድ እያላችሁ ስትመላለሱ ብቻ ነዉ፡፡ በክረምት ዕረፍት ለሁለት ወራት ወደ ቤተሰብ ስትሄዱ የክረምት ተማሪዎች ይተኩ ነበር፡፡ አሁን ግን  ማንም ተማሪ የለም፡፡ የትምህርት ቤት/ተቋም ትልቁ የውበት ምንጭና ሕይወት ተማሪ ነዉ፡፡

ውድ ተማሪዎቻችን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ  አደገኛነትንና አሳሳቢነትን ለናንተ ለማስረዳት አልሞክርም፡፡ አደራችሁን ለማለት የምፈልገዉ ራሳችሁን እንድትጠብቁና እያንዳንዱ የማኅበረሰብ አካል ከቤተሰቦቻችሁ ጀምሮ ራሱን እንዲጠብቅ የምትችሉትን ሁሉ እንድታደርጉ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ወደ  ፈጣሪያችን በፀሎት መፅናት ይኖርብናል፡፡

ውድ ተማሪዎቻቸን ከትምህርት ጋር ላለዉ ጉዳይ በልዩ ልዩ ሚዲያዎች በኩል  መረጃ እንደምታገኙ  እየተገነዘብኩ እየተሠሩና እየታሰቡ ያሉ  ሁኔታዎችን እንደሚከተለው እገልፃለሁ፡፡

1. የድህረ ምረቃ ትምህርትን በተመለከተ የተማሪ ብዛት መጠነኛ በመሆኑና አብዛኛው ተማሪ በከተማና የኢንተርኔት አገልግሎት ሊያገኝ የሚችልበት አከባቢ ላይ በመሆኑ የ2012 የ2ኛ ሴሚስቴር ትምህርት ሳይቋረጥ በኦንላይን ቀጥሏል፡፡ የፈተናና ግምገማ ሥራዎችንም በዚሁ መልክ በማስኬድ የሴሚስቴሩን ትምህርት እንደሚያጠናቅቁ ታስቦ ትምህርት እየተሰጠና የመመረቂያ ምርምር ሥራዎችም እየተሠሩ ይገኛል፡፡

2. የቅድመ ምረቃ ትምህርትን በተመለከተ የ1ኛ ዓመት ተማሪዎች በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት መሠረት የተዘጋጀውን የሁሉም ኮርሶች ሞጁል ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዌብሳይት ላይ በመውሰድ መጠቀም ይጠበቅባቸዋል፡፡ የ2ኛ ዓመትና ከዚያ በላይ ያሉ ተማሪዎችም ኮርስ ማቴሪያል እንደዚሁ በዩኒቨርሲቲዎች ተዘጋጅቶ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዌብሳይት ላይ ለማስቀመጥ እየተሠራ በመሆኑ ተማሪዎች ወስደዉ መጠቀም ይገባቸዋል፡፡  የኮርስ ማቴሪያሎችን በዚህ መልክ በማግኘት ተማሪዎች እያነበቡ በመቆየት የቫይረሱ ወረርሽኝ ችግር ከቆመ በኋላ ተማሪዎች ወደየዩኒቨርሲቲያቸዉ ስመለሱ ስያጠኑ የቆዩትን የኮርስ ይዘቶች መምህራን ባጠረ ጊዜ ዉስጥ በማጠቃለያ ክለሳ መልክ በማስተማርና ፈተና በመስጠት የኮርሶቹ የመማር ማስተማር ሂደት ይጠናቀቃል ተብሎ ታስቦ እየተሠራ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ሁሉም ተማሪዎች የኮርስ ማቴሪያሎችን በማግኘት ሙሉ ጊዜያችሁን በንባብ ላይ እንድታሳልፉ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡

ውድ ተማሪዎቻችን በዚህ ሂደት የሚችሉትን የመገናኛ ዘዴ ሁሉ በመጠቀም ከዩኒቨርሲቲዉ መምህራን ለማግኘት የምፈልጉትን ድጋፍ ከመጠየቅ እንዳትቆጠቡ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ የዩኒቨርሲቲው መምህራንና የአካዳሚክ አመራር አካላትም ተማሪዎቻችንን የኮርስ ይዘቶችን በማንበብም ሆነ የፕሮጀክት ሥራዎችን በማከናወን ሂደት ከእኛ የሚሹትን ድጋፍ ለማድረግ በምንችለው አማራጭ ሁሉ በመጠቀም ጥረት እንድናደርግ አደራ እላለሁ፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በትምህርት አቀራረቡ ዙሪያ አቅጣጫ እየሰጠ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር እየሠራ ሲሆን የኮቪድ-19 ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በምርምርና በማኅበረሰብ አገልግሎት ዩኒቨርሲቲዎችን እያስተባበረ በመምራት ሙሉ ጊዜ ሰጥቶ እየሠራ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎች፣ መምህራንና የህክምና ባለሙያዎችም በያሉበት አከባቢ ልዩ ልዩ ተግባራትን በመፈጸም የወረርሽኙን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ የአስተዳደር ሠራተኞችና ተማሪዎች በሙሉ በያለንበት ሁሉ ራሳችንን ከመጠበቅ አንስቶ ሌሎችም ራሳቸዉን እንዲጠብቁ የምንችለውን ሁሉ በማድረግ ለሕዝባችንና ሀገራችን ደህንነት የበኩላችንን እንድናበረክት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና በራሴ ስም ከልብ አደራ እላለሁ!!

ውድ ተማሪዎቻችን ከፈጣሪ ጋር በመሆን ከመንግስትና ከጤና ባለሙያዎች የሚተላለፉ መመሪያዎችን በትኩረት ተግባራዊ ካደረግን ይህንን ፈተና እንሻገራለን፡፡ ወደምንወደውም የመማር ማስተማርና ምርምር ሥራ በዩኒቨርሲቲያችን ግቢዎች ሆነን በሙሉ ጊዜ የምንሠራበት ወቅት ላይ እንደርሳለን፡፡ 

ከሁሉም በላይ  ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይጠብቅ!!!


ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት