አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለጎፋ ዞን አስተዳደር ኮሮናቫይረስን ለመከላከልና ለማከም የሚውል የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለጎፋ ዞን አስተዳደር የዞኑና የከተማው አመራሮች እንዲሁም የተለያዩ የአካባቢው ማኅበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት የኮሮናቫይረስን ለመከላከልና ለማከም የሚውሉ የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶችን ግንቦት 5/2012 ዓ/ም አበርክቷል፡፡

የተደረገው ድጋፍ ለሳኒታይዘር ዝግጅት የሚውል 500 ሊትር አልኮል፣ 5 የሙቀት መለኪያዎች፣ ሰርጂካል የፊት መሸፈኛ ጭንብሎችና የእጅ ጓንቶች እንዲሁም ሌሎች የቫይረሱን ተጠቂዎች ለማከም የሚረዱ መድኃኒቶች ያካተተ መሆኑን የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺይፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ ገልፀዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት ይህንን ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በሀገራችን ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ በአርባ ምንጭ ከተማና በጋሞ ዞን ወረዳዎች ግንዛቤ በመፍጠርና ማኅበረሰቡን ከማንቃት አንስቶ ለህክምና ባለሙያዎች ሥልጠናዎችን መስጠትና የተለያዩ የምግብና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፎችን የማድረግ ሚናውን እየተወጣ ቆይቷል፡፡ ለጎፋ ዞን የተደረገው ድጋፍም የዚሁ ሥራ አካል ሲሆን ዩኒቨርሲቲው ያደረገው ድጋፍ ችግሩን ሙሉ በሙሉ ሊቀርፍ የሚችል ባለመሆኑ ባለሃብቶችና ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ፕሬዝደንቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የጎፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የሠላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ጅፋሬ በበኩላቸው የዞናቸው አስተዳደር በሽታው ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን እንደቆየ ተናግረው ዩኒቨርሲቲው ያደረገው ድጋፍ የዞኑን አስተዳደር ጥረት በእጅጉ የሚደግፍ ነው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ላደረገው ድጋፍ በዞኑ አስተዳደርና በጎፋ ሕዝብ ስም ምስጋናቸውን ያቀረቡት አቶ ብርሃኑ ይህ ክፉ ጊዜ እስኪልፍ ድረስ ዩኒቨርሲቲው የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ከቁሳቁስ ድጋፉ በኋላ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ፣ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺይፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ ከጎፋ ዞን አመራሮች ጋር በመሆን ከሳውላ ከተማ ከተወጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የሴቶችና ወጣቶች ተወካዮች ጋር በቫይረሱ መከላከልና ቁጥጥር ዙሪያ ሰፊ ውይይት ያካሂደዋል፡፡ በተጨማሪም ዶ/ር ዳምጠው ከዞኑ አመራሮችና የተለያዩ ኅብረተሰብ ተወካዮች ጋር በመሆን በሳውላ ከተማ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች በመገኘት በበሽታው ዙሪያ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ዶ/ር ታምሩ ሽብሩም በቡልቂ ከተማ ተገኝተው ከኮሌጁ የህክምና መምህራን እንዲሁም ከቡልቂ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጋር በመሆን በቡልቂ ከተማ ገበያ በመገኘት የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ሠርተዋል፡፡

ሁለቱም ኃላፊዎች በመልዕክታቸው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አደገኛና ገዳይ በሽታ መሆኑን ስለሆነ ኅብረተሰቡ ከጤና ባለሙያዎችና ከመንግስት የሚተላለፉ መመሪያዎችን ባለመዘናጋት ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት አጽንዖት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት