የዩኒቨርሲቲው ካውንስል መስከረም 20/2013 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው የ2013 በጀት ዓመት ዓመታዊ ዕቅድ ላይ ውይይት በማድረግ አፅድቋል፡፡ ለዕቅዱ ማስፈጸሚያ ለመደበኛ እና ለካፒታል በድምሩ ብር 1,594,367,000 ተመድቧል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደተናገሩት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዕውቀት፣ በክሂሎት፣ በአመለካከት እንዲሁም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ታግዘው ጥናትና ምርምር በማካሄድ ለእውናዊው ዓለም ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ መስጠት የሚችሉና በመልካም አስተሳሰብ የዳበሩ ዜጎችን የመቅረጽ ተልዕኮ አንግበው ይሠራሉ፡፡ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር፣ በምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት እንዲሁም በአስተዳደር ዘርፎች የበጀት ዓመቱን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ዶ/ር ዳምጠው አሳስበዋል፡፡

የስትራቴጂክ ዕቅድ ዝ/ት/ግ/ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አስፋው ደምሴ በበኩላቸው የ2013 በጀት ዓመት ዕቅድን ለማሳካት ተቋማዊ አደረጃጀት፣ ግብዓትና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ለማሻሻል፣ የመሠረታዊ አሠራር ለውጥና የሚዛናዊ ውጤት ተኮር ሥርዓትን ለመተግበር የሚያስችል ሥርዓት ተዘርግቶ የሚተገበር ሲሆን አፈጻጸሙንም በየሩብ ዓመቱ በመገምገም ማሻሻያዎች እንደሚደረጉ ተናግረዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በመማር ማስተማር በተለያዩ የሙያ መስኮች በቅድመ ምረቃ በመደበኛ የትምህርት መርሃ-ግብር 76 እና መደበኛ ባልሆነ የትምህርት መርሃ-ግብር 38 ፕሮግራሞች፣ በ2ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች በመደበኛ የትምህርት መርሃ-ግብር ከ99 ወደ 102 እና በመደበኛ ባልሆነ የትምህርት መርሃ-ግብር ከ29 ወደ 31 ለማሳደግ ታቅዷል፡፡ እንዲሁም በ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች በመደበኛ የትምህርት መርሃ ግብር ከ22 ወደ 24 ለማሳደግ መታቀዱን አቶ አስፋው ገልጸዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በመማር ማስተማር ዘርፍ ክትትል ቤተ-ሙከራዎች፣ ወርክሾፖች፣ ኮምፒውተር ቤተ-ሙከራዎችና ቤተ-መጻሕፍት ደረጃቸውን መጠበቃቸውን ማረጋገጥ፣ የትምህርት ግብዓቶች እንዲሟሉ ማድረግ፣ የትምህርት መርሃ-ግብሮች ተቀባይነት እንዲኖራቸው የሚያስችሉ ሥራዎችን ማከናወን፣ የልየታና የልኅቀት ሥራዎችን የሚመራ ኮሚቴ ማቋቋም፣ BSC ዕቅድን እስከ መምህራን ድረስ አውርዶ በመፈራረም ወደ ሥራ እንዲገባ ማድረግ፣ የድኅረ-ምረቃና የተከታታይና ርቀት ትምህርት ፕሮግራሞች በዕቅዱ መሠረት እንዲተገበሩ ማድረግ፣ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ለዩኒቨርሲቲው በኃላፊነት የተሰጠውን የቅድመ ምረቃ የውሃ ፕሮግራሞች የሥርዓተ ትምህርት ክለሳ በማጠናቀቅ ማስረከብና የበይነ-መረብ ትምህርትን ከፊት-ለፊት መማር-ማስተማር ጋር አቀናጅቶ ለመሥራት ቅድመ ሁኔታዎችን የሚያመቻች ኮሚቴ በማዋቀር መመሪያ ማዘጋጀት በበጀት ዓመቱ ለማከናወን ከታቀዱ ዋና ዋና ተግባራት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

አቶ አስፋው ባቀረቡት ሪፖርት አንደተመለከተው ማለቅ ሲገባቸው ያላለቁ ፕሮጀክቶችን ክትትል ማድረግና በሚጠናቀቁበት ሁኔታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት፣ በኮቪድ ዙሪያ እየተሠሩ ያሉ የምርምርና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራዎችን በመደገፍ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል እንዲቻል መሥራት፣ እየተገባደዱ ያሉ የማኅበረሰብ ፕሮጀክቶችን ለባለድርሻ አካላት ማስተላለፍ፣ የበጎ አድራጎት፣ የማዕድ ማጋራት፣ የአካባቢ ጥበቃና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ማስፈፀሚያ ሥራዎችን በተቀናጀ መልኩ መሥራት እንዲሁም የምርምርና የማኅበረሰብ ፕሮግራም በጀቶችን ለኮሌጆችና ለምርምር ማዕከላት

መደልደልና በጀቱን ማውረድ በምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ በ2013 በጀት ዓመት ለማከናወን ከታቀዱ ዋና ዋና ተግባራት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በዩኒቨርሲቲው በበጀት ዓመቱ መደበኛ በጀት ብር 1,144,367,000.00 እና ካፒታል በጀት ብር 450,000,000 በድምሩ ብር 1,594,367,000 ሆኖ ፀድቋል፡፡ በበጀት ድልድሉ ለመማር ማስተማር 582,455,300.00፣ ለምርምር 51,496,600.00፣ ለሥራ አመራርና አስተዳደር 324,644,600.00፣ ለማማከርና ማኅበረሰብ አገልግሎት 54,920,500.00 እና ለተማሪ አገልግሎት 130,850,000.00 ተደርጓል፡፡ በጀቱ ውጤታማነትንና ቀልጣፋነትን በሚያረጋግጥ መልኩ የሚፈፀምበትን አቅጣጫና ሥርዓት በመከተል በፋይናንስና በጀት አስተዳደር የበጀት አጠቃቀም ውጤት ተኮር መርህ መሠረት ተግባራዊ ይሆናል፡፡

በዕቅድ ግምገማው የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና የካውንስል አባላት ተገኝተዋል፡፡

ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት