ላለፉት ሦስት ዓመታት እየጣለ ባለው ዝናብ አማካኝነት እየገባ ባለው ከፍተኛ ደለል ምክንያት የዓባያና ጫሞ ሐይቆች ከመጠን በላይ መሙላታቸውና ከብዙ ዓመታት በኋላ ሐይቆቹ ዳግም መገናኘታቸው ተገልጿል፡፡ ላለፉት 45 ዓመታት ተቋርጦ የቆየው ጫሞ በሰገን በኩል የሚያደርገው ፍሰትም ጥቅምት 16/2013 ዓ/ም ዳግም ጀምሯል፡፡

የውሃ ሥነ-ምኅዳር ተማራማሪው ዶ/ር ፋሲል እሸቱ እንደገለጹት ዓባያ ሐይቅ ከጫሞ ሐይቅ በአማካይ የ67 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ሐይቁ ከመጠን በላይ በሚሞላ ጊዜ በዋሎ ረግረጋማ ሥፍራ በኩል ኩልፎ ወንዝን በመቀላቀል ወደ ጫሞ ሐይቅ የሚገባ ሲሆን ጫሞ ሐይቅም በሰገን በኩል ወደ ሰርማሌ ወንዝ እንደሚተነፍስ የምርምር ድርሳናት ያመላክታሉ፡፡ ነገር ግን እ.አ.አ ከ1975 ጀምሮ ላለፉት 45 ዓመታት የጫሞ ሐይቅ በሰገን በኩል ወደ ሰርማሌ የሚያደርገው ፍሰት ተቋርጦ የቆየ ሲሆን እ.አ.አ አቆጣጠር ከ1980-2013 ድረስ ደግሞ የጫሞና የዓባያ ሐይቆች ግንኙነት የተቋረጠ በመሆኑ ምክንያት የጫሞ ሐይቅ መጠን እየቀነሰና ጨዋማነቱ እየጨመረ እንደመጣ የተለያዩ የምርምር ውጤቶች እንደሚጠቁሙ ዶ/ር ፋሲል ተናግረዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

እንደ ዶ/ር ፋሲል ገለፃ በአሁኑ ሰዓት ዓባያ ወደ ጫሞ እያደረገ ባለው ከፍተኛ ፍሰት ምክንያት በጫሞ ሐይቅ ላይ ያልነበረው የእንቦጭ አረም በሐይቁ ላይ እየተስፋፋ ከመሆኑ ባሻገር የኩልፎ ወንዝ ወደ ሐይቁ በሚገባበት አከባቢ ያለው የሐይቁ ከፍል የዓባያ ሐይቅን ቀለም እየያዘ በመምጣቱ ሐይቁ ላይ ጉዳት እየደረሰበት ይገኛል፡፡ በዚህም ምክንያት የጫሞ ሐይቅ ዓሳ ምርት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል ብለዋል፡፡ በጉዳዩ ላይም ትኩረት ተሰጥቶ የማይሠራ ከሆነ ከ 5 ዓመት በኋላ ጫሞም እንደ ዓባያ የምግብ ሠንሰለት ሥርዓቱ ተዛብቶ የዓሳ ምርቱ በከፍተኛ ሁኔታ ሊቀንስ ይችላል የሚል ሳይንሳዊ ትንበያ እንዳለ ዶ/ር ፋሲል አመላክተዋል፡፡

ሁለቱም ሐይቆች በከፍተኛ ሁኔታ እንደሞሉና በአከባቢያቸው ባሉ የአርሶ አደር ማሳዎችና መሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ መሆናቸውን የጠቀሱት ዶ/ር ፋሲል ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት እያጣለ ባለው ዝናብ ሳቢያ ወደ ሐይቆቹ እየገባ በሚገኘው ደለልና ጎርፉ እየጠረገ ወደ ሐይቆቹ በሚያስገባቸው የሙዝ ተክልና ሌሎች ቁሶች ምክንያት ነው፡፡

እ.አ.አ 2025 ይህ ክስተት ሊከሰት እንደሚችልና በሐይቆቹ ዙሪያ በተሠሩ የመንገድ፣ አየር መንገድና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ከዚህ ቀደም በሠሩት የምርምር ሥራቸው መተንበያቸውን የተናገሩት ዶ/ር ፋሲል ነገር ግን ክስተቱ ከትንበያው ጊዜ ቀድሞ እየታየ መሆኑ በከፍተኛ ሁኔታ ተፈጥሮ መዛባቱንና መጎዳቱን ያሳያል ብለዋል፡፡ አሁን ላይ በሁለቱ ሐይቆች ዙሪያ ያሉ የእርሻ መሬቶች፣ ረግረጋማና አሸዋማ ቦታዎች እንዲሁም የመዝናኛ ቦታዎች ጭምር በውሃ ተውጠው የሐይቁ ክፍል መሆናቸውን የገለጹት ዶ/ር ፋሲል ይህም ሐይቆቹ ወደ ቀድሞ ቦታቸው እየተመለሱ መሆናቸውን አመላካች ነው ብለው እንደሚያምኑና ከአርባ ምንጭ አዲስ አበባ የሚወስደው ዋና የአስፋልት መንገድና የአርባ ምንጭ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፍያ ጭምር ይህ ዕጣ ሊደርሳቸው ስለሚችል የሚመለከተው አካል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ለሐይቆቹና በሐይቆቹ ዙሪያ ላለው ብዝሃ ሕይወት መጎዳት ዋነኛው ምክንያት በሐይቆቹ ተፋሰሶች ያለው የደን ሀብት መመናመን፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ በስፋት አለመሠራት፣ በሐይቆቹ ዙሪያ ያለው በፈር ዞን በአግባቡ አለመከለሉና መታረሱ መሆኑን ዶ/ር ፋሲል ተናግረዋል፡፡

ሐይቆቹንና በሐይቆቹ ሥር ያለውን ብዝሃ ሕይወት መታደግ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ መሆን እንዳለበት የተናገሩት ዶ/ር ፋሲል በዋናነት በሐይቆቹ ተፋሰስ ላይ ሳይንሳዊ ጥናትና ምርምርን መሠረት አድርጎ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ መሥራት እንዲሁም በሐይቆቹ ዙሪያ የጠፉትን እንደ ደንገልና ሶኬ የመሳሰሉ እጽዋትን መልሶ መተካት ይገባል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በጫሞ ሐይቅ ላይ የተከሰተው የእንቦጭ አረም ሳይስፋፋ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባም ተመራማሪው ጠቅሰዋል፡፡ በተለይ ወደ ጫሞ ሐይቅ በየዓመቱ የሚገባው ከ3 ሚሊየን ቶን በላይ ደለል አብዛኛው ደንብሌ አከባቢ ከሚገኙ ቀበሌያት የሚመጣ መሆኑ መለየቱን የጠቀሱት ተመራማሪው እነዚሁ ቀበሌያት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በትኩረት ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡

ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች ችግሮችን ለመቅረፍ ዩኒቨርሲቲው ከIUC ፕሮግራምና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ከምርምርና ጥናት ሥራዎች ባሻገር በጫሞ ሐይቅ ዙሪያ ደንገል በመትከል የሐይቁን ዙሪያ ወደ ነበረበት የመመለስ፣ ለዓሳ መራቢያ የሚሆን ቦታ በጫሞ ሐይቅ ላይ የመከለል እና እንቦጭን ከአስጋሪዎች ጋር በመሆን የማስወገድ ሥራ በትብብር በመሥራት ሐይቆቹን ለመታደግ የሚያግዙ ሥራዎችን እየሠራ ነው፡፡ ችግሩ በዩኒቨርሲቲው ጥረት ብቻ የሚቀረፍ ባለመሆኑ የዞኑ መንግሥት፣ ነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ፣ እነዚህን የተፈጥሮ ሀብቶች መሠረት ያደረጉ ሆቴሎችና ሎጆች እንዲሁም ሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በተለይ አርሶ አደሩ ሐይቆቹንና በዙሪያቸው ያለውን ብዝሃ ሕይወት ለመታደግ በትብብር ሊሠሩ እንደሚገባ ዶ/ር ፋሲል አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት