ዩኒቨርሲቲው ለ7 ወራት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተቋርጦ የቆየውን የቅድመ ምረቃ ትምህርት ለማስጀመር በመማር ማስተማሩ ዘርፍ አስፋላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ ገልፀዋል፡፡

እንደ ም/ፕሬዝደንቱ ገለፃ ዩኒቨርሲቲው የኮሮና ቫይረስ ከመከሰቱ ጋር ተያይዞ ተቋርጦ የቆየውን የገፅ ለገፅ ትምህርት ለማስጀመር ከመንግሥት የተላለፉ መመሪያዎችን መሠረት በማድረግ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ አሁን ላይ የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ-ሙከራዎች፣ ቤተ-መጽሐፍት፣ የኮምፕዩተር ላብራቶሪዎች ኮቪድ-19ን ባገናዘበ መልኩ ለተማሪዎች ዝግጁ ተደርገዋል ብለዋል፡፡ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን በ3ት ዙር እንደሚቀበል የተናገሩት ዶ/ር የቻለ በመጀመሪያው ዙር 4,574 ተመራቂ ተማሪዎችን ተቀብሎ በሁለት ወራት ወስጥ አስተምሮ ያስመርቃል ብለዋል፡፡

አሁን ላይ በሁሉም የዩኒቨርሲቲው ኮሌጆች ለተመራቂ ተማሪዎች ኮርስ የሚሰጡ መምህራን የኮርስና የክፍለ ጊዜ ድልድል መደረጉን የገለፁት ም/ፕሬዝደንቱ ተማሪዎች እንደመጡ አንድም ቀን ሳይባክን የመማር ማስተማሩ ሥራ ይጀመራል ብለዋል፡፡ የመማር ማስተማሩ ሥራ ከገፅ ለገፅ ትምህርት በተጨማሪ በʻE-learningʼ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ ለመማር ማስተማሩ መሳለጥ ሲባል ከላይ እስከ ታች ባሉት የዩኒቨርሲቲው መዋቅሮች የመማር ማስተማሩን ሥራ የሚከታተልና የሚገመግም ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ እንደሚሠራ ዶ/ር የቻለ ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ የመማር ማስተማሩን ሥራ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የተቀመጡ መመሪያዎችን ጠብቆ ለማስቀጠል ዩኒቨርሲቲው ለሚያደርገው ጥረት መላው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ የራሱን ሚና እንዲወጣ ዶ/ር የቻለ አበክረው አሳስበዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመጪው ሳምንት የቅድመ ምረቃ ተመራቂ ተማሪዎቹን ለመቀበል ጥሪ ማስተላለፉ ይታወቃል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት