የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት በጋሞ ዞን ጨንቻ ወረዳ ዶርዜ ቀበሌ የቴክኒክና ሙያ እና የዩኒቨርሲቲ ትምህርት አጠናቀው ሥራ ላጡና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚኖሩ እማወራ ሴቶች ከቀርከሃ ምርት የተለያዩ ቁሳቁሶችን ማምረትና መሸጥ የሚያስችል ሥልጠና ከጥቅምት 16/2013 ዓ.ም ጀምሮ እየሰጠ ይገኛል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደገለጹት መቀመጫውን በአዲስ አበባ አድርጎ በምሥራቅ አፍሪካ በቀርከሃ ምርት ላይ ጥናት ከሚያደርገው ‹‹International Bamboo & Rattal Organization›› (INBRA) የተሰኘ ግብረ ሠናይ ድርጅት ጋር በመጻጻፍ በተገኘ 650 ሺ ብር ድጋፍ በአካባቢው የራሳቸው ገቢ የሌላቸውን እማወራ ሴቶች በሦስት ቡድን በማዋቀር ሥልጠናው እየተሰጠ ነው፡፡ ድርጅቱ ለቆላና ለደጋ አካባቢ የሚስማሙ የቀርከሃ ዝርያዎች በማምጣት በዞኑ ደጋማና ቆላማ አካባቢዎች ለመትከል ማቀዱን ዶ/ር ተክሉ ተናግረዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የቴክኒክና ሙያ እና የዩኒቨርሲቲ ትምህርት አጠናቀው ሥራ ያጡና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ ሴቶች የገቢ ምንጭ እንዲያገኙ ማስቻል የሥልጠናው ዓላማ መሆኑን የሥልጠናው አስተባባሪ ረ/ፕ/ር ፋሲል እሸቱ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በጋሞ ደጋማ አካባቢዎች የቀርከሃ ዛፍ በመትከል የአፈርና የአየር ንብረት ጥበቃን ማጠናከርና ለቀርከሃ ምርት አቅራቢዎች ገበያ ማፈላለግ ነው፡፡

የፕሮጀክቱ አባል የሆኑት አቶ ዓይናለም ጎቸራ እንደገለጹት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ እማወራዎችን ችግር ለመቅረፍ የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ አገልግሎት ከግብረ ሠናይ ድርጅቱ ባገኘው ድጋፍ በመጀመሪያ ዙር ለሠላሳ ሴቶችና ለአራት ወንዶች ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ በቀጣይም በተመሳሳይ ሁኔታ በሁለት ዙሮች ሥልጠናው የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከሠልጣኞች መካከል የዶርዜ ቀበሌ ነዋሪና የሁለት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ሳባ ሰለሞን የ10ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ትዳር የያዙ ሲሆን ባለቤታቸው ወደ አዲስ አበባ በመሄዳቸው ልጅ የማሳደግ ኃላፊነትን ለብቻ በመሸከም ትምህርታቸውን ለመቀጠል አልቻሉም፡፡ የራሳቸው ገቢ የሌላቸው በመሆኑ ሲቸገሩ የቆዩት ወ/ሮ ሳባ በፕሮጀክቱ በመታቀፍ ሥልጠና እየወሰዱ ይገኛል፡፡ በሥልጠናው የሶፋ ወንበር፣ አልጋ፣ የኩርሲ ወንበርና የምግብ ጠረጴዛ ከቡድን አባላት ጋር በመሆን መሥራት መቻላቸውን ገልጸው ከሥልጠናው በኋላ በግልም ይሁን በማኅበር በመደራጀት ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የጨንቻ ዙሪያ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም ኢንኮ ከቀርከሃ ተክል ከመኖሪያ ቤትና የአጥር ሥራ ውጪ ዘመናዊ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችን መሥራት እንደሚቻል በሥልጠናው ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡ አስተዳዳሪው ሥልጠናውን የሰጡ አካላትን በወረዳው ስም አመስግነው ቀጣይነት እንዲኖረውም ጠይቀዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት