2ኛ ዙር የደምባ ተፋሰስ አፈር መሸርሸር ቅነሳና የሸክላ ሠሪዎችን ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ላይ ያተኮረ የምርምር ፕሮጀክት አጀማመር ውይይት በጋሞ ዞን ዲታ ወረዳ ጥቅምት 21/2013 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ 2011 ዓ/ም ላይ የተጀመረ ሲሆን ለሦስት ዓመታት የሚዘልቅ ነው፡፡ በመጀመሪያው ዓመት መረጃዎችን የመሰብሰብና መሬት ላይ ያለውን እውነታ የመለየት ሥራ የተሠራ ሲሆን በሁለተኛው ዓመት የአፈር ጥበቃ ሥራው ሲሠራ ሸክላ ሠሪዎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ ተለይቷል፡፡ በ2013 በጀት ዓመት ሙሉ በመሉ ወደ ትግበራ የተገባ መሆኑን ዶ/ር ስምዖን ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮች መሬት በጎርፍ እንዳይጎዳ ከማድረጉ ባሻገር የዲታ ወረዳ ከፍተኛ ቦታዎች የዓባያና ጫሞ ሐይቆች ገባር ወንዞች መነሻ ቦታ ስለሆኑ በገባር ወንዞች አማካኝነት ወደ ሐይቆቹ የሚገባው ደለልም ይቀንሳል ብለዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የምርምር ዳይሬክቶሬት ቺፍ ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተርና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ተሾመ ይርጉ በበኩላቸው በሸክላ ሥራ ላይ የተሰማሩ በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች በማኅበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ዝቅተኛ አመለካከት መቀየር፣ በባህላዊ መንገድ የሚያመርቱትን የሸክላ ሥራ በዘመናዊ መልክ እንዲሠሩ ሥልጠና መስጠት፣ የተለያዩ ቅርጻ-ቅርጾችን የሚያወጡ መሣሪያዎችን ገዝቶ መስጠት፣ ከወረዳው አመራሮች ጋር በመወያየት የመሥሪያና የመሸጫ ቦታ ማመቻቸትና የገበያ ትስስርን በመፍጠር ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ ማድረግ የፕሮጀክቱ ዋነኛ ተልዕኮ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው የሸክላ ሥራ ባለሙያ የሆኑት አቶ አንዷለም አሸናፊ ማኅበረሰቡ ለሸክላ ሥራ ያለው አመለካከት ዝቅተኛ መሆኑን አስታውሰው በቂ የእርሻ መሬት እንደሌላቸውና በሽክላ ሥራ የሚያገኙት ገቢም አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ልጆቻቸውን አስተምረው ለትልቅ ደረጃ ማብቃት እንዳልቻሉ የሚናገሩት ግለሰቡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የጀመረው ፕሮጀክት ሕይወታቸውን ይቀይራል የሚል ተስፋ መሰነቃቸውን ገልጸዋል፡፡

የዲታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አንተነህ ቱቴ በደምባ ተፋሰስ አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮች መሬታቸው በጎርፍና በናዳ በተደጋጋሚ እንደሚጎዳ ተናግረው ፕሮጀክቱ ይህንን ጉዳት ለመከላከል ብሎም የሸክላ ሠሪዎችን የኢኮኖሚ አቅም ከማጎልበት አንፃር ፋይዳው ጉልህ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡

የዲታ ወረዳ ኢንተርፕራይዞችና ኢንደስትሪ ትስስር ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ካርታ ክንፉ በበኩላቸው በሸክላ ሥራ የሚተዳደሩና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በማደራጀት፣ የመሥሪያና የመሸጫ ቦታ በማዘጋጀት እንዲሁም ብድር የሚያገኙበትን ሁኔታ በማመቻቸት ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ በጽ/ቤታቸው ስም ቃል ገብተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት