የዩኒቨርሲቲው የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ ከጂኦግራፊና አካባቢ ጥናት ትምህርት ክፍል ጋር በመሆን ዓለም አቀፉን የጂ አይ ኤስ ቀን ‹‹Progressing GIS›› በሚል መሪ ቃል ኅዳር 9/2013 ዓ/ም በፓናል ውይይት አክብሯል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በመክፈቻ ንግግራቸው ባለንበት 21ኛው ክ/ዘመን የጂኦ ስፓሻል መረጃዎችና ቴክኖሎጂ ከመሠረተ ልማት፣ ከኮሚዩኒኬሽን፣ ከኃይልና ከሃይድሮሎጂ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመቅረፍ ያላቸው ፋይዳ ጉልህ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ በዚህ ረገድም ዩኒቨርሲቲው የጂ አይ ኤስና ጂኦ ኢንፎርማቲክስ ቤተ-ሙከራ በማስገንባትና ከተለያዩ በዘርፉ ከሚሠሩ ተቋማት ጋር በመተባበር በዘርፉ የሥልጠና፣ የመረጃና የምርምር ማዕከል ለመሆን እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ የጂኦ ስፓሻል ሥርዓት በዩኒቨርሲቲያችን መዘርጋቱ ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን ለሚያደርገው ጉዞ ፋይዳው ጉልህ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ንጉሴ ታደገ እንደተናገሩት የጂኦ ስፓሻል መረጃዎች ለፈጠራ ሥራዎች፣ ለምርምር፣ ለግብርና፣ ለግንባታና ለቢዝነስ ነክ ሥራዎች የግድ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ከዚህም አንፃር ጂ አይ ኤስ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና ፈጠራዎችን ከማሳለጥ አንፃር ጠቀሜታው ጉልህ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ለዘርፉ ዕድገትና ልማት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ዶ/ር ንጉሴ አመላክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሪሞት ሴንሲንግ ምርምርና ልማት ኃላፊ ዶ/ር ብርሃን ገሠሠ ‹‹Geoformation: Guiding Our Future Path›› በሚል ርዕስ ባሰሙት ንግግር አሁን ባለንበት የቴክኖሎጂ ዘመን የጂኦ ስፓሻልና ጂ አይ ኤስ መረጃዎች ለአካባቢና ለሥነ-ምኅዳር ጥናት፣ ለመሠረተ ልማት ግንባታና ዕቅድ የተለያዩ ትልልቅ የግድብ፣ የኃይል ማመንጫ፣ የባቡር መንገዶች ሥራ ሚናቸው ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር መረጃዎቹ የአየር ንብረት ለውጥ ትንተና ለማከናወን፣ ጎርፍ፣ ድርቅና የመሬት መንቀጥቀጥ የመሳሰሉ አደጋዎችን ቀድሞ ለመከላከል የሚያገለግሉ ሲሆን መረጃዎቹ ወታደራዊና የደኅንነት ሥራ ላይም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በሀገራችን የሚስተዋሉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የጂኦ ስፓሻል መረጃና ቴክኖሎጂ ያላቸው ሚና ትልቅ በመሆኑ በዘርፉ የሚሠሩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የምርምር ማዕከላት በትብብር ሊሠሩ ይገባል ሲሉ አጽንዖት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡

የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሙሉጌታ ደበሌ በበኩላቸው በርካታ ሀገራት የጂ አይ ኤስ ቴክኖሎጂን ተጠቅመው የመሠረተ ልማትና የድንበር ማካለል ሥራዎችን እንዲሁም የተፈጠሮ አደጋ ችግሮቻቸውን እንደፈቱበት ተናግረው ቴክኖሎጂው በሀገራችን ያላደገ በመሆኑ ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ይህን ቴክኖሎጂ ለማሳደግና በዘርፉ ጠንካራ የሥልጠና፣ የመረጃና የምርምር ማዕከል ለመሆን እየሠራ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ሙሉጌታ ለዚህም ይረዳ ዘንድ ከተለያዩ በዘርፉ ከሚሠሩ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር እየሠራን እንገኛለን ብለዋል፡፡ መሰል በዓላት መከበራቸውም በዘርፉ የክሂሎትና የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ ይረዳል ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የጂ አይ ኤስና ሪሞት ሴንሲንግ መምህር አቶ ደንበል ቦንታ ጂ አይ ኤስን በመጠቀም የአኗኗር ዘይቤያችንን የሚያቃልሉና ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ሥራዎችን መሥራት እንደሚቻል ተናግረው በግላቸው ጂ አይ ኤስን በመጠቀም ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መረጃ ልውውጥ የሚሆን መተግበሪያ መሥራታቸውን ተናግረዋል፡፡ መተግበሪያው የበሽታውን

ሥርጭት በዕድሜ፣ በፆታና በቦታ በመለየት በዝርዝር ማቅረብ የሚችል ሲሆን ይህም በመረጃ ልውውጥ ጊዜ የሚከሰቱ ስህተቶችን የሚያስቀር ነው ብለዋል፡፡

የጂኦግራፊና አካባቢ ጥናት ትምህርት ክፍል ኃላፊ መ/ር አፈራ አዝመራው እንደተናገሩት ትምህርት ክፍሉ ከ600 መቶ በላይ ተማሪዎችን ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ተቀብሎ እያስተማረ ሲሆን ትምህርት ክፍሉን ወደ ጂኦግራፊና ጂኦ ኢንፎርማቲክስ ት/ቤት ደረጃ ከፍ ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡ የጂ አይ ኤስ ቀን መከበሩም ከተለያዩ በዘርፉ ከሚሠሩ ተቋማት ጋር ልምድና ተሞክሮ እንድንለዋወጥ ከማድረጉ ባሻገር ከተቋማቱ ጋር በትብብር እንድንሠራም ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ይረዳናል ብለዋል፡፡

በበዓሉ ላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ከኢትዮጵያ ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት እና ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የተወጣጡ የዘርፉ ምሁራንና የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት