ዩኒቨርሲቲው በሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን ላይ ሕግ የማስከበር እርምጃ እየወሰደ ለሚገኘው የሀገር መከለከያ ሠራዊት ከተቋሙ የ3 ሚሊየን ብር፣ ከመምህራንና የአስተዳደር ኃላፊዎች ከደመወዛቸው 50 በመቶ እና ከአስተዳደር ሠራተኞች እንዲሁ ከደመወዛቸው 30 በመቶ ድጋፍ እንዲደረግ ወስኗል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የሀገሪቱ አለኝታና ጠባቂ በሆነው የሀገር መከለከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የተፈፀመውን አሳፋሪ ጥቃት ተከትሎ መንግሥት በሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን ሕግ የማስከበር እርምጃ በመደገፍ ከዩኒቨርሲቲው 3 ሚሊየን ብር፣ ከመምህራንና የአስተዳደር ኃላፊዎች ከደመወዛቸው 50 በመቶ እና ከአስተዳደር ሠራተኞች ከደመወዛቸቸው 30 በመቶ ድጋፍ እንዲደረግ የዩኒቨርሲቲው ካውንስል መወሰኑን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም በዩኒቨርሲቲው ሁሉም ካምፓሶች ለሠራዊቱ የደም ልገሳ መርሃ ግብር ከሰኞ ኅዳር 14/2013 ዓ/ም ጀምሮ ይካሄዳል ብለዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ኃላፊ መ/ር ካሱ ጡሚሶ በበኩላቸው ከሀገሩ አልፎ በተለያዩ ሀገራት ሰላም በማስከበር ጥንካሬውንና ጀግንነቱን ባስመሰከረው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ በሕወሓት ቡድን የተፈፀመው ክህደት በታሪክ ተሰምቶ የማያውቅ መሆኑን ገልጸው ይህም ኢትዮጵያ በጣሊያን በተወረረች ጊዜ ለጣሊያን ወግነው የኢትየጵያን አርበኞች ከወጉ ባንዳ ኢትዮጵያዊያን ድርጊት ጋር የሚስተካከል ነው ብለዋል፡፡

በሠራዊቱ ላይ የተፈፀመው ጥቃትና እየተወሰደ ያለው እርምጃ ከሕግ አንፃር ያለውን አንድምታ በተመለከተ የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት በዩኒቨርሲቲው የሕግ ት/ቤት ዲን መ/ር ደርሶልኝ የኔአባት የሕወሓት ቡድን በመካላከያ ሠራዊቱ ላይ የፈፀመው ጥቃትና በሠራዊቱ አባላት ላይ ያደረሰው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እንዲሁም በማይካድራ በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈፀመው ዘር ተኮር ጭፍጨፋ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በጦር ወንጀለኝነት የሚያስጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ቡድኑ የፈፀመው ድርጊት የሀገሪቱን ሕጎች ብሎም የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ድንጋጌዎችንና ስምምነቶችን የሚጥስ መሆኑን መ/ር ደርሶልኝ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብም በወቅታዊ የሀገሪቱ ሁኔታ፣ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ታሪክ፣ ተልዕኮ እንዲሁም በሠራዊቱ ላይ የተፈፀመው ጥቃትና ሠራዊቱ በሕገ-ወጡ ቡድን ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ ከሕግ አንፃር ባለው አንድምታ ዙሪያ መነሻ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት አካሂዷል፡፡

በመጨረሻም ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን በመከላከያ ሠራዊቱ ሰሜን ዕዝ ላይ የፈፀመውን ጥቃትና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በጽኑ የሚያወግዝና የሀገር መከላከያ ሠራዊት በዚህ ሕገ-ወጥ ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ የሚደግፍ ባለ 5 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማስደመጥ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

በውይይቱ የዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላት፣ የተማሪዎች ኅብረት አመራሮችና የሰላም ፎረም አባላት ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት