የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ IUC ፕሮጀክት ‹‹በደቡብ ኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ በዓባያና ጫሞ ተፋሰስ የመሬት መራቆትን መቀነስ ለዘላቂ የመሬት አጠቃቀም›› በሚል መሪ ቃል ጥቅምት 20/ 2013 ዓ/ም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ዓውደ ጥናት አካሂዷል፡፡

ከቤልጂየም ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ለሚደረገው ምርምር የፕሮጀክት 4 አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ደረጀ ፀጋዬ እንደገለጹት ፕሮግራሙ በዓባያና ጫሞ ሐይቆች ተፋሰስ ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን መሠረት አድርጎ ከሚያከናውናቸው የምርምር ፕሮጀክቶች አንዱ በሆነው የመሬት መራቆት ላይ ያተኮረ ሲሆን ዓላማውም በምርምር የተገኙ ውጤቶችን ለባለድርሻ አካላት በማሳወቅ ውይይት ማድረግ፣ በቀጣይ ተፋሰሱን የማከምና የማዳን ሥራዎች የሚሠሩበትን ሂደቶች ማመቻቸት እንዲሁም የተገኙ ግኝቶች ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆኑ ማስቻል ነው፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በዓውደ ጥናቱ በቤልጂየምና በሀገር ውስጥ በሚማሩ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ከመሬት መራቆት ጋር የተያያዙ 5 የጥናት ውጤቶች ቀርበዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የናቹራል ሪሶርስ ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል መምህር እና በቤልጂየም ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪ ልዑልሰገድ በላይነህ የቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ የዓባያና ጫሞ ሐይቆች መሙላትና በተፋሰሶቹ የመሬት ናዳና ደለል ሁኔታዎችን ይዳስሳል፡፡ ጥናቱ በጋሞ ዞን 6 ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ 93 ቀበሌያት የሚያካልል ሲሆን ከ7,300 በላይ ገደሎች ለጥናቱ ተለይተዋል፡፡

በጥናቱ እንደተመለከተው በተፋሰሶቹ በዝናብ አማካኝነት የሚከሰተው የመሬት መሸርሸር /gully erosion/ ለሐይቆቹ በደለል መሞላት ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ለጫሞ ሐይቅ በደለል መሞላት የሲሌና ኤልጎ ወንዞች እንዲሁም ለዓባያ ሐይቅ ባሶና ሻፌ ወንዞች ትልቁን አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆኑን ጥናቱ ያሳያል፡፡

የመሬት ናዳ በርካታ ሰዎችን ከመኖሪያ ስፍራቸው የሚያፈናቅልና ለብዙዎች የሞት አደጋን የሚያስከትል በመሆኑ አደጋዎቹ በአብዛኛው የሚከሰቱበት የጋሞ ከፍታማ ቦታዎች ላይ የማይታረሱ ተራራማ ቦታዎችን አለማረስ እንዲሁም እርከንና የተለያዩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን መሥራት ችግሮቹን ለመቀነስ እንደሚረዳ መ/ር ልዑልሰገድ ባቀረቡት ጽሑፍ ጠቅሰዋል፡፡

ሁለተኛዋ ጥናት አቅራቢ የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርት እና በቤልጂየም ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪ ትዝታ እንዳለ የመሬት መራቆት ከቦታ ወደ ቦታ መልኩን እየቀያየረ የሚከሰት፣ በምግብ ዋስትና በኩል ትልቅ ችግር እያስከተለና በየጊዜው እየጨመረ ያለ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢነቱ ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በጋሞ ዞን ከሲሌ እስከ ገረሴ ባለው ቆላማ አካባቢ አፈሩ ጨዋማነት ያለውና የገበሬውን ምርት በጣም የሚቀንስ ሲሆን ለዚህም መፍትሄ አርሶ አደሩ ውሃን በማንጣፈፍ ማጠጣት እንዳለበትና አፈሩን በመሸፈንና ውሃ የሚወዱ አትክልቶችን በመትከል መከላከል እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡ በቆላውም ሆነ በደጋው አካባቢ ያለው አርሶ አደር ሊከሰት የሚችለውን ችግር አስቀድሞ በማወቅ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ የዓባያና ጫሞ ተፋሰስ ችግሮች በአሁኑ ወቅት እጅግ አሳሳቢ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረው ፕሮጀክቱ ሲያልቅ ተጨባጭ የሆነ ለውጥ መሬት ላይ ሊታይ ይገባል ብለዋል፡፡ በተፋሰሱ የወንዞችና የሐይቆች ውሃ መጠን መጨመር፣ የእርሻ ቦታዎችና አስፋልት መንገዶች በውሃ መጥለቅለቅ እንዲሁም የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ እየተከሰተ ያለው የመሬትና የብዝሃ ሕይወት መራቆት አፋጣኝ መፍትሔና የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ የችግሩን አሳሳቢነት ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ በማዳረስ በጋራ መሥራት የሚገባ መሆኑን ዶ/ር ስምዖን ተናግረዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ የቀረቡት ጽሑፎች እንደሚያሳዩት በጋሞ ደጋማ አካባቢዎች ላይ ያለው የመሬት አጠቃቀም የመሬት መራቆት፣ የመሬት መንሸራተት፣ ናዳ፣ የሐይቆች መሙላትና ውሃው ሐይቁን ለቆ ወደ እርሻና መኖሪያ ቤቶች ላይ መምጣት እንዲሁም ከእርሻው ታጥቦ ወደ ውሃው የሚገባውን ኬሚካል መነሻ አድርጎ የውሃ ኬሚስትሪ ሲቀየር እርሱን ተከትሎ የእንቦጭ አረም መዛመት እና በውሃ ውስጥ ያሉ ነፍሳትና ሌሎች የብዝሃ ሕይወት አካላት ላይ ጉዳት እያስከተለ ነው፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት