የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ምሩቃን ማኅበር፣ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እና ሬጂስትራርና አልሙናይ ዳይሬክቶሬት በመተባበር ለውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህራንና የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች የውሃ ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም በሚያስችሉ አዳዲስ ሶፍትዌሮች ዙሪያ ከጥቅምት 30 - ኅዳር 04/2013 ዓ/ም የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የማንችስተር ዩኒቨርሲቲ የውሃ ዘርፍ ተመራማሪ የሆኑት የቀድሞው የዩኒቨርሲቲው ምሩቅና አሠልጣኝ ዶ/ር ሮቤል ጥላዬ እንደገለጹት በውሃ ሀብቶች ዕቅድና አያያዝ፣ በኮምፒውተር ፕሮግራም እንዲሁም በሌሎች ከዚህ ቀደም በተሰጡ ሥልጠናዎች መሻሻሎች ታይተዋል፡፡ የታዩ ለውጦችን ለማጠናከር፣ የውሃ ሀብት ብክነትንና በዘርፉ አላስፈላጊ ወጪዎችን ለመቀነስ፣ ቀልጣፋና ፈጣን አሠራርን ለመዘርጋትና ቀጣይነትን ለማረጋገጥ ሥልጠናው ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡ አያይዘውም በውጭ አገር የሚገኙ ሌሎች በርካታ ኢትዮጵያዊያንና የቀድሞ የዩኒቨርሲቲው ምሩቃን ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ ለመሥራት ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸው ሠልጣኛቹ ከሥልጠናው ካገኙት ዕውቀትና ክሂሎት በተጨማሪ በራሳቸው ጊዜ ልምምድ በማድረግ በውሃ ቴክኖሎጂ ዘርፍ የምርምር ክሂሎትን በማሳደግ የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ዶ/ር ሮቤል አሳስበዋል፡፡

የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማል በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በኢንስቲትዩቱ ሥር ለሚገኙ መምህራን በውሃ ግድቦችና በወንዝ ተፋሰስ አስተዳደር፣ በአየር ንብረት ለውጥ ሞዴሎችና የምልከታ መሣሪያዎችን በሚመለከት ሥልጠና እንደተሰጠ ገልጸዋል፡፡ የአሁኑ ሥልጠና በአዳዲስ ሶፍትዌሮች ዙሪያ የሚያተኩር፣ የውሃ ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል እና የመምህራንንና የድኅረ ምረቃ ተማሪዎችን የምርምር ክሂሎት ለማሳደግ ጉልህ አስተዋፅዖ ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ድኅረ-ምረቃ ት/ቤት ዲን ዶ/ር ዳኛቸው ዳንኤል በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና ሶፍትዌሮች ዙሪያ በተሰጠው ሥልጠና ውጤት ላይ በመመርኮዝ በቀጣይ በውሃ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ለሚገኙ መምህራንና የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች በተግባር የተደገፈ ሥልጠና ለመስጠት ዳይሬክቶሬቱ ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው በውሃ ቴክኖሎጂ ዘርፍ የውሃ ሀብት ክፍፍልን ሚዛናዊ ለማድረግና አዳዲስ ሶፍትዌሮችን ለመፍጠር የሚያስችል በመሆኑ ቀጣይነት እንዲኖረው ጠይቀዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት