የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተቋማዊ ለውጥና መልካም አስተዳደር ዳይሬክቶሬት በውስጣዊና ውጫዊ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ ኅዳር 11 /2013 ዓ/ም ውይይት አካሂዷል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ውስጥና በአካባቢው ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚፈቱበትን መንገድ በተለይም በተቋሙ በተማሪ ሥነ-ምግባር ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ለመፍታት ውይይቱ መዘጋጀቱን የተቋማዊ ለውጥና የመልካም አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በኃይሉ በፈቃዱ ተናግረዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከተማሪዎች ሥነ-ምግባር ጋር የተያያዙም ሆነ ሌሎች ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮችን ለመፍታት በሙሉ አቅም ሊሠራ ይገባል፡፡

በየካምፓሱ ዙሪያ እና በዋናው ግቢ በር የጫት መሸጫ፣ የሺሻና የመጠጥ ቤቶች እንዲሁም የምሽት ክለቦች መኖራቸው ለተማሪዎች ሥነ-ምግባር መበላሸት ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸው በውይይቱ ተነስቷል፡፡ ከከተማው ማዘጋጃ ቤትና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ ሚዛናዊ አስተሳሰብ ያለው፣ የሚማርና የሚመራመር ትውልድ ማፍራት ተገቢ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

በውይይቱ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲውና የአካባቢው የጸጥታና ደኅንነት አባላት፣ የምክር ቤት አባላት፣ የማዘጋጃ ቤትና የዞኑ የጸጥታና ደኅንነት መምሪያ ኃላፊ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የወጣት ተወካዮችና የዩኒቨርሲቲው አማካሪዎች ተገኝተዋል፡፡