በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ድጋፍ የተከናወነው የአርባ ምንጭ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ማስፋፊያ ግንባታ ተመረቀ

በዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አገልግሎት ድጋፍ በወዜ ቀበሌ በሚገኘው አርባ ምንጭ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት የተከናወነው የአንድ ብሎክ ሕንፃ የማስፋፊያ ክፍሎች ግንባታ ተጠናቆ ኅዳር 19 /2013 ዓ/ም ተመርቋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደገለጹት አርባ ምንጭ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ያለበትን የክፍል ጥበት ችግር ለመቅረፍና የተማሪ ቅበላ አቅሙን ለማሳደግ በ2008 ዓ/ም ለዩኒቨርሲቲው ባቀረበው የድጋፍ ጥያቄ መሠረት ዩኒቨርሲቲው የት/ቤቱን ችግር ከግምት በማስገባት 4 ክፍሎችን የያዘ አንድ ብሎክ ግንባታ ለማከናወን የሚረዳ የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡ የቁሳቁስ ድጋፉ በገንዘብ ሲተመን 1 ሚሊየን ብር የሚሆን ነው፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የትምህርት ቤቱ ር/መምህር አቶ አዳነ ገዛኻኝ እንደገለጹት በግንባታ ግብዓት ግዥ ሂደት መጓተት፣ በቁሳቁስ ዋጋ ንረት፣ በግንባታ ተቋራጮችና ሌሎች ችግሮች የማስፋፊያ ግንባታው 5 ዓመታትን ፈጅቷል፡፡ ክፍሎቹ በዚህ ጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸው በተለይም ከኮቪድ-19 በሽታ ጋር ተያይዞ የገጠመንን የመማሪያ ክፍል ጥበት የሚቀርፍ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይም ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመደጋገፍ የት/ቤቱን የቤተ-መጻሕፍት፣ የቤተ-ሙከራና የመማሪያ ክፍል ዴስክና ጥቁር ሠሌዳ ችግር ለማቃለል ማቀዳቸውንም ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው አርባ ምንጭ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤትና ሌሎችም በዩኒቨርሲቲው አቅራቢያ የሚገኙ ት/ቤቶችን በዕውቀትና በቁሳቁስ በማገዝ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ የድርሻውን እንደሚወጣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተናግረዋል፡፡

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙ ተጋባዥ እንግዶች ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ የሚያከናውናቸው ሥራዎች የሚያስመሰግኑ እንደሆኑ ገልጸው ከመንግሥት አካላት ጋር በመተባበር ት/ቤቱን ይበልጥ ለማልማትና ምቹ ለማድረግ የት/ቤቱ አመራር ማኅበረሰቡ የሚሳተፍበትን መንገድ እንዲያመቻች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በአካባቢው የሚስተዋሉ መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ተደራሽነቱን በማስፋትና በትኩረት ሊሠራ ይገባል ሲሉም ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል፡፡

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት፣ የሥራ ክፍል ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲው አማካሪ ምክር ቤት አባላት፣ የወዜ ቀበሌ አመራሮች፣ የወላጅ ተማሪና መምህር (ወተመ) ኮሚቴዎች፣ የት/ቤቱ ርዕሰ መምህር፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሠራተኞችና የት/ቤቱ ተማሪዎች ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡