የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የምርምር ንድፈ-ሃሳቦችን ገመገመ

የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በመምህራን የተዘጋጁ የምርምር ንድፈ-ሃሳቦችን የዘርፉ ተመራማሪዎች በተገኙበት ከኅዳር 8 - 9/2013 ዓ/ም ገምግሟል፡፡

ጎርፍና የጎርፍ መከላከያ ዘዴዎች፣ የውሃ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች የከርሰ ምድር ውሃ አወጣጥና አጠቃቀም፣ የመስኖ ሥራ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም የውሃ ኃይል ማመንጫ ቦታዎችን መለየትና የተሻሉትን መጠቀም ከቀረቡ የምርምር ንድፈ-ሃሳብ ይዘቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ዩኒቨርሲቲዎች ከመማር ማስተማር ሥራ ጎን ለጎን ምርምሮችን እያካሄዱ ከሌሎች ዓለም አቀፍ የትምህርት ተቋማት ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆኑ መንግሥት በየዓመቱ ከፍተኛ በጀት እንደሚመድብ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማል ተናግረዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም ከመንግሥት የሚሰጠውን በጀት በመጠቀም ምርምሮችን በስፋት ለማካሄድ አቅዶ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት 60 በመቶ ማስተማር፣ 25 በመቶ ምርምርና 15 በመቶ የማኅበረሰብ አገልግሎት የሥራ አፈጻጸም እንደሚመዘን ቀደም ሲል ከኢንስቲትዩቱ መምህራን ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ዶ/ር አብደላ ጠቅሰው መምህራንለሚያከናውኑት ምርምር ከፍተኛ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በምርምር ንድፈ-ሃሳቦቹ ዝግጅት ከ90 በላይ መምህራን የተሳተፉና 32 ንድፈ-ሃሳቦች ቀርበው በዘርፉ ባለሙያዎች የተተቹ ሲሆን 16ቱ ተመርጠዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት