ሥነ-ትምህርትና ሥነ-ባህርይ ሳይንስ ትምህርት ቤት የአዕምሮ ጤና፣ ሥነ-ልቦናና ማኅበራዊ አገልግሎትን በተመለከተ ሥልጠና ሰጠ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥነ-ትምህርትና ሥነ-ባህርይ ሳይንስ ትምህርት ቤት ከተማሪዎች ጋር ቀጥታ ግንኙነት ላላቸው የሥነ-ልቦና፣ ጋይዳንስና ካውንስሊግ እና የዜሮ ፕላን ባለሙያዎች፣ የተማሪዎች አገልግሎት ሠራተኞች እንዲሁም የተማሪዎች መኝታ ቤት፣ የምግብ  አገልግሎት፣ የሰላም ፎረምና የደኅንነትና ጥበቃ አስተባባሪዎች የአዕምሮ ጤና፣ ሥነ ልቦናና ማኅበራዊ   አገልግሎት አሰጣጥንን በተመለከተ ከኅዳር 10-11/2013 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሥነ-ትምህርትና ሥነ-ባህርይ ሳይንስ ትምህርት ቤት ዲን አቶ አንለይ ብርሃኑ እንደገለጹት ባለፉት ስምንት ወራት ተማሪዎችና አጠቃላይ ማኅበረሰቡ ከCOVID-19 በሽታ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ማኅበራዊና ሥነ-ልቦናዊ ጫናዎች ውስጥ ገብተዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ከተማሪዎች ጋር ቀጥታ ግንኙነት ላላቸው ባለሙያዎች ጫናውን ሊቀንስ በሚያስችል መልኩ ግንዛቤ በመስጠት ተማሪዎች ቀድሞ በነበረው ሁኔታ እንዳይጎዱና በትምህርታቸው ላይ ተፅዕኖ እንዳይፈጥር በሚያስችል መልኩ ሥልጠናው መሰጠቱን አቶ አንለይ ተናግረዋል፡፡

በትምህርት ቤቱ የሥነ-ልቦና ሳይንስ መምህር አቶ ማርቆስ ካንኮ በበኩላቸው አስገዳጅ ማቆያ (ኳራንቲን) መግባት፣ በበሽታው ምክንያት ቤተሰብን ማጣትና የመሳሰሉ ከCOVD 19 በሽታ ጋር የተያያዙ ችግሮች ያጋጠሟቸው ተማሪዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ ካጋጠማቸው ጭንቀትና የስሜት ውጥረት ተላቀው ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ ታስቦ የተዘጋጀ ሥልጠና ነው ብለዋል፡፡

የአእምሮ ጤና፣ የሥነ-ልቦናና ማኅበራዊ አገልግሎት ምንነት፣ የድጋፍ ቡድኑ መዋቅርና አደረጃጀት፣ አገልግሎቱ የሚሰጥበት ዘዴና ለተማሪዎች ተደራሽ የሚደረግበት መንገድ የሥልጠናው ይዘቶች ናቸው፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት