የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቤኔፊት ሪያላይዝ (BENEFIT REALISE) ፕሮግራም ከደራሼ፣ ምዕራብ ዓባያ፣ ቁጫ እና ዛላ ወረዳዎች 16 ቀበሌያት ለተወጣጡ የግብርና ባለሙያዎች ከታኅሣሥ 1-2/2013 ዓ.ም በወላይታ ሶዶ የአሠልጣኞች ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ቤኔፊት ሪያላይዝ ፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር መብራቱ ዓለሙ እንደተናገሩት የአሠልጣኞች ሥልጠናው የተዘጋጀው የግብርና ባለሙያዎቹ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የድኅረ-ምርት አያያዝና የተቀናጀ የተባይ መከላከል ላይ በቂ ዕውቀት ጨብጠው አርሶ አደሩን እንዲያሰለጥኑና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በየጊዜው የሚከሰቱትን ተባይ፣ አረም እንዲሁም የምርት ብክነት እንዲቆጣጠሩ ለማስቻል ነው፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ሥልጠናው የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አንፃር ከአርሶ አደሮች ጋር በቅንጅት በመሥራት ከመዝራት እስከ መሰብሰብና ወደ ኢኮኖሚ ማስገባት ድረስ ያለው ሂደት ውጤታማ እንዲሆን የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

የተቀናጀ የሰብል ጥበቃና የተባይ መከላከያ ዘዴዎችን በተመለከተ ሥልጠና የሰጡት የግብርና ኮሌጅ ዲንና ተመራማሪ ዶ/ር ብርሃኑ ለማ በማሳ የሚዘሩ ሰብሎች፣ የጓሮ አትክልት፣ ፍራፍሬና ጥራጥሬን የሚያጠቁ የሀገር ውስጥና ከውጪ ሀገር የሚመጡ ተባዮች ምርትና ምርታማነትን የሚቀንሱ፣ ጥራትን የሚያሳጡና የምግብ ዋስትና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የተቀናጀ የሰብል ጥበቃና የተባይ መከላከያ ዘዴዎችን ከአካባቢ ጋር በማዋሃድና ምንም ዓይነት ጉዳት የማያደርሱ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ተፅዕኖውን ለመቀነስና ጤንነቱ የተጠበቀ ምርት ላይ ለመድረስ የጥናት ዝርዝር ውጤቶች ለሠልጣኞች ይሰጣል፡፡ አርሶ አደሩ ፀረ- ተባይን እንደ መጨረሻ አማራጭ እንዲጠቀም ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እንደሚሠራም ዶ/ር ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት ከሥልጠናው ትልቅ ግንዛቤ ማግኘታቸውንና በቀጣይ ከአርሶ አደሩ ጋር በመቀናጀት ወደ ተግባር የሚቀይሩት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት