የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝደንትነት ውድድር ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ገለጻ ቀረበ

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትነት እና ለምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንትነት ኅዳር 21/2013 ዓ/ም ባወጣው ክፍት የሥራ መደብ ማስታወቂያ መሠረት የውድድሩ አካል የሆነው ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ገለጻ ታኅሣሥ 7/2013 ዓ/ም ለሴኔቱ ቀርቧል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ገለጻውን ያቀረቡት በአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዘርፍ የተወዳደሩት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ፣ ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ፣ ዶ/ር መሠረት ፋንታ፣ ዶ/ር ትዕዛዙ ገብሬና ዶ/ር አቡኑ አጥላባቸው ሲሆኑ በምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዘርፍ ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ፣ ዶ/ር ዲቃሱ ኡምቡሼ እና አቶ በኃይሉ መርደኪዮስ ናቸው፡፡

በቀረበው የየዘርፉ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት ማብራሪያዎች የተሰጡ ሲሆን የተነሱት ጉዳዮች ከተቋማዊ ዘርፍ ግንባታ ጋር ያላቸው ተዛማጅነት እንዲሁም ጥንካሬና ድክመታቸው ላይ ግምገማ ነክ ነጥቦች ተነስተዋል፡፡

በመቀጠልም የሴኔቱ ድምፅ የመስጠትና ምርጫ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል፡፡ በምርጫው ሂደት አንድ የሴኔትና የአስመራጭ ኮሚቴ አባል በየዘርፉ ውድድር አንድ ጊዜ ብቻ ድምፅ መስጠት የሚችል ሲሆን በየዘርፉ ከተወዳደሩት ዕጩዎች አንዱን ብቻ በመምረጥ በተዘጋጀው ነጭ ወረቀት ላይ ስሙን ጽፎ እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም ምርጫ የተካሄደባቸው ወረቀቶችና አዳራሽ ውስጥ የተገኙት የመራጮች ቁጥር ተመሳሳይ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በመጨረሻም በተደረገው የድምፅ ቆጠራ በየዘርፉ ላሉ ተወዳዳሪዎች ያገኙት ነጥብ በዚያው ሰዓት ይፋ ሆኗል፡፡

ሂደቱን ለማስፈፀም አስመራጭ ኮሚቴ የነበሩት የቦርድ ተወካይ፣ የሴኔት ተወካይ፣ የመምህራን ተወካይ፣ የአስተዳደር ሠራተኞች ተወካይ እንዲሁም የተማሪዎች ኅብረት ተወካይ አባላት ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት የመጀመሪያው ዙር የውድድር መግለጫ ወጥቶ ተወዳዳሪዎች ቅሬታ ካላቸው ቅሬታቸውን የሚያቀርቡበት ሂደት ላይ እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት