የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ 87 የሕክምና ዶክተሮችን በመጪው ቅዳሜ ያስመርቃል

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለ7ኛ ዙር ያሠለጠናቸውን 87 የሕክምና ዶክተሮችን በመጪው ቅዳሜ ታኅሣሥ 24/2013 ዓ/ም በድምቀት ያስመርቃል፡፡ ከተማራቂዎቹ መካከል 32ቱ ሴቶች ሲሆኑ 55ቱ ወንዶች ናቸው፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ የሕክምና ትምህርት በባህሪው ከበድ ያለና በርከት ያሉ ፈተናዎች የሚታለፉበት መሆኑን ጠቅሰው በተለየ መልኩ የዘንድሮ ተመራቂዎች ላለፉት ዘጠኝ ወራት ኮቪድ-19ን ለመከላከልና ለማከም በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሕይወታቸውን ጭምር ሰውተው ሲሰሩ የቆዩ ናቸው ብለዋል፡፡ ይህም የዘንድሮ ተመራቂዎችን ከሌሎች ጊዜያት በተለየ መልኩ የተፈተኑና ፈተናውንም በጽናት ያለፉ በመሆናቸው አሸናፊዎች ናቸው ሲሉ ገልፀዋቸዋል፡፡

ለተማራቂዎች፣ ለተመራቂ ቤተሰቦችና መምህራን ‹‹እንኳን ደስ አላችሁ!›› ሲሉ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ዶ/ር ታምሩ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የፌዴራል የሥራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት አባላትና አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅሰዋል፡፡ ተመራቂዎችና የተመራቂ ቤተሰቦች ወደ ምረቃው ስፍራ ሲመጡ አስፈላጊውን የኮቪድ-19 መከላከል ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ዶ/ር ታምሩ አሳስበዋል፡፡ የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ማኅበረሰብም ለተመራቂ ዶክተሮች በስልጠና ወቅት ላደረገው ድጋፍና ትብብር ዶ/ር ታምሩ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት