አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለ7ኛ ጊዜ ያሠለጠናቸውን የሕክምና ዶክተሮች አስመረቀ

ዩኒቨርሲቲው ለ7ኛ ጊዜ ያሠለጠናቸውን 87 የሕክምና ዶክተሮች ታኅሣሥ 24/2013 ዓ/ም በደማቅ ሁኔታ አስመርቋል፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከል 32ቱ ሴቶች ናቸው፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወደ ሀገራችን ከገባበት ጊዜ ጀምሮ እንደ ሌሎች የሀገሪቱ የጤና ባለሙያዎች ሁሉ የዩኒቨርሲቲያችን የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህራንና የዛሬ ተመራቂ ዶክተሮች ወረርሽኙን ለመከላከል ግንዛቤ በማስጨበጥ እንዲሁም ለኅብረተሰቡ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ያለ እረፍት ሲያገለግሉ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ሂደት በኮቪድ-19 በሽታ ተይዘው ከዳኑት መካከል መምህራንና ተመራቂ ተማሪዎች ይገኙበታል ብለዋል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

 

ዶ/ር ዳምጠው ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት ለኅብረተሰቡ የጤና መሻሻል በመንግሥት በኩል እየተደረገ ለሚገኘው ርብርብ ስኬታማነት የእናንተ መመረቅ ጉልህ አስተዋፅኦ የሚኖረው በመሆኑ በተመረቃችሁበት ዘርፍ በሙሉ አቅማችሁ በማገልገል ለሀገራችን እድገትና ብልፅግና ከፍተኛ ሚና መጫወት ይጠበቅባችኋል ብለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የገበዩትን ዕውቀትና ክሂሎት በነባራዊው የሥራ ዓለም ከሚያካብቱት ልምድ ጋር በማዋሐድ ብቁ ባለሙያ እንዲሆኑም አሳስበዋል፡፡

የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ዴኤታ እና የዕለቱ የክብር እንግዳ ወ/ሮ ሳህረላ አብዱላሂ ዓለማችን ብሎም ሀገራችን አስከፊውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እየተፋለመች ባለችበት ወቅት መመረቃቸውና በቀጣይም እንደ ትናንቱ ሁሉ ለፍልሚያው ግንባር ቀደም ሆነው መሰለፋቸው የዛሬ ተመራቂዎችን ለየት የሚያደርጋቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ወ/ሮ ሳህረላ አክለውም ማኅበረሰባችን ከፈጣሪ በታች የጤና ባለሙያዎችን የሚያምን በመሆኑ ባለን አቅም ሁሉ ልናግዘው፣ የሚገጥመውን የጤናና ተያያዥ ችግሮች ልንፈታለትና ደስታው የእኛም ደስታ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡ የዚህ ዓይነት አገልግሎት ራስን ማብቃት፣ ራስን ማዘጋጀት፣ መራራትና ለሙያው መሰጠትን የሚጠይቅ፣ ሰዋዊ ባህሪያትን የያዘና ከምንም በላይ ድርጊትን የሚሻ በመሆኑ ተመራቂዎች ሕዝባችሁንና ሀገራችሁን በሙያዊ ኃላፊነትና ፍቅር እንደምታገለግሉ እምነቴ ነው ብለዋል፡፡

ኮቪድ-19 ያልተጠናቀቀ ስጋታችን በመሆኑ ተመራቂ ተማሪዎችም ሆኑ መላው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ትኩረት በመስጠት ስለ ወረርሽኙ የተሳሳቱ አመለካከቶችን መቀየር፣ የማስክ ተጠቃሚነት እንዲጨምር ማድረግ እንዲሁም ሌሎች እርምጃዎችን ማጠናከርና ቀጣይ በሚደረገው ሀገራዊ ርብርብ ውስጥ በብቃት መሳተፍ እንደሚገባው ወ/ሮ ሳህረላ በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡

3.89 በማምጣት በእጅግ ከፍተኛ ማዕረግ የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚ የሆነው ተመራቂ ዶ/ር ቡዜር መሐመድ የሕክምና ትምህርት በባህሪው ሙሉ ጊዜን የሚፈልግና ማንበብና መዘጋጀትን የሚጠይቅ በመሆኑ አብዛኛው ትኩረቴ ትምህርት ላይ ብቻ ነበር ብሏል፡፡ ወደ ሕክምናው ዘርፍ ወስነን እንደመግባታችን ራሳችንን ከቴክኖሎጂው ጋር በየጊዜው በማሳደግና የሥራ

ተነሳሽነታችንን በማጎልበት በታማኝነትና በጥንቃቄ ኅብረተሰቡን ልናገለግል ይገባል ብሏል፡፡ በቀጣይም በሕክምናው ዘርፍ ያለውን ዕውቀት ለማሳደግ በማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታሎች መሥራት እንደሚፈልግ ገልጿል፡፡

3.57 በማምጣት ከአጠቃላይ ሴት ተማሪዎች በ1ኛነት ልዩ ተሸላሚ የሆነችው የማዕረግ ተመራቂ ዶ/ር ማህሌት እሸቱ ፈታኝ ጊዜያትን ባሳልፍም በትምህርቴ ውጤታማ በመሆኔ ተደስቻለሁ ብላለች፡፡ ሴት ልጅ እችላለሁ ብላ ካመነችና ከሠራች ውጤታማ እንዳትሆን የሚያግዳት ነገር እንደሌለ ገልጻ በቀጣይ በእናቶች ጤና ላይ መሥራት እንደምትፈልግ ተናግራለች፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት