አርባ ምንጭ የኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች ለ33ኛ ጊዜ አስመረቀ

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ 3,141 ወንድ እና 1,717 ሴት እንዲሁም 1 የሦስተኛ ዲግሪ በአጠቃላይ 4,858 ተማሪዎች ጥር 18/2013 ዓ/ም አስመርቋል፡፡

ተማሪ ተሜ አለኸኝ ከግብርና ሳይንስ ኮሌጅ በአግሪካልቸራል ኢኮኖሚክስ 4.00 በማምጣትና 37A+ በማስመዝገብ የዋንጫ ተሸላሚ ሲሆን ተማሪ ዓለምወርቅ ግድይሁን ከግብርና ሳይንስ ኮሌጅ በሩራል ዴቭሎፕመንት እና አግሪካልቸራል ኤክስቴንሽን 3.94 በማምጣትና 27A+ በማስመዝገብ ከሴት ተመራቂዎች በአንደኛነት የወርቅ ሀብል ተሸልማለች፡፡   ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በተጨማሪም ከየትምህርት ክፍላቸው 1ኛ ለወጡ የመጀመሪያ ዲግሪ ምሩቃን ሽልማት፣ ከኢንስቲትዩት፣ ከኮሌጅና ከት/ቤት 1ኛ ለወጡ የወርቅ ሜዳልያ፣ ከኢንስቲትዩት፣ ከኮሌጅና ከት/ቤት 1ኛ ለወጡ ሴት ምሩቃን ልዩ ሽልማት ተበርክቷል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትርና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት ሀገራችን በዕውቀት፣ በክሂሎት እንዲሁም በመልካም አስተሳሰብና ሥነ-ምግባር የተገነቡ ቅን፣ ሚዛናዊና ጠንካራ ባለሙያ የሆኑ ዜጎች የምትፈልግ በመሆኑ በትምህርት ዘመናችሁ ያገኛችሁትን ዕውቀት፣ ክሂሎትና ልምድ በመጠቀም ራሳችሁን፣ ቤተሰባችሁን፣ ማኅበረሰባችሁንና ሀገራችሁን ለማገልገል በተማራችሁበት መስክ ጠንካራ ሠራተኛ መሆን ይገባችኋል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በመክፈቻ ንግግራቸው ተመራቂዎች በየተመደቡበት የትምህርት መስክ በስኬት አጠናቀው ለምረቃ በመብቃታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ከዩኒቨርሲቲው በገበዩት ዕውቀትና ክሂሎት ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን በመልካም ሥነ-ምግባር እንዲያገለግሉ አደራ ብለዋል፡፡

የዋንጫ ተሸላሚው ምሩቅ ተሜ አለኸኝ በስኬቱ እጅግ መደሰቱን ተናግሮ በተመረቅሁበት መስክ ኅብረተሰቤንና ሀገሬን በታማኝነት አገለግላለሁ ብሏል፡፡

ከሴቶች ከፍተኛውን ውጤት ያመጣችሁ ተማሪ ዓለምወርቅ ግድይሁን ጊዜን በአግባቡ መጠቀምና በዓላማ መንቀሳቀስ ስኬታማ የሚያደርግ መሆኑን ተናግራለች፡፡

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር፣ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ ም/ሰብሳቢ፣ የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባላት፣ ተጋባዥ እንግዶች፣ የጋሞ ዞንና የዩኒቨርሲቲው አመራሮች እንዲሁም የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት