የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲንና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ፈቃዱ ማሴቦ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ዩኒቨርሲቲ ኖርዌይ ከሚገኘው በርጌን ዩኒቨርሲቲ ጋር እየሠራ የሚገኘው የፕሮጀክት ሥራ በመጀመሪያ ዙር አመርቂ ውጤት በማስመዝገቡ ዩኒቨርሲቲው ለ2ኛ ዙር የʻNorwegian Program for Capacity Development in Higher Education and Research for Development/NORHEDʼ ፕሮጀክት ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ


የመጀመሪያው ዙር ፕሮጀክት እ.ኤ.አ ከ2013-2020 ዓ.ም የቆየ ሲሆን በʻMedical Entromologyʼ እና ʻVecter Controlʼ ትምህርት ፕሮግራም ከበርጌን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር 30 የ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ማስመረቁን ዶ/ር ፈቃዱ ተናግረዋል፡፡ እንደ አስተባባሪው ገለጻ በተጨማሪም የቤተ-ሙከራ ግብዓቶች የተሟሉ ሲሆን የʻPCRʼ ማሽን በ192,000 (አንድ መቶ ዘጠና ሁለት ሺህ) የኖርዌይ ክሮንና ʻHILUXʼ መኪና በ30,350 (ሠላሳ ሺህ ሦስት መቶ ሃምሳ) ዶላር ተገዝተዋል፡፡ በወባ፣ በሌሽማኒያሲስ፣ በብጫ ወባና ሌሎች በሽታዎች መከላከያና መተላለፊያ መንገዶች ላይ ትኩረት በማድረግ ጥናቶች መካሄዳቸውንም አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡

በፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ዙር ከ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎችና ተመራማሪዎች 50 በመቶ የሚሆኑትን ሴቶች ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ዲኑ ገልጸው በፕሮጀክቱ የታቀፉ ሴቶች ደመወዝ የሌላቸው በወር 2,000.00/ሁላት ሺህ/ ብር ደመወዝ ያላቸው ደግሞ በሴሚስቴር 3,000.00/ሦስት ሺህ/ ብር ድጋፍ ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በትምህርት ላይ ባሉበት ወቅት ለሚወልዱ ሴቶች ፕሮጀክቱ በየ3 ወሩ 6,000.00/ ስድስት ሺህ/ ብር በአጠቃላይ 18,000.00/አስራ ስምንት/ ሺህ ብር ድጋፍ ለማድረግ አቅዶ አንዲት ተማሪ ብቻ በዕድሉ ተጠቃሚ መሆኗን አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ፈቃዱ በ2ኛ ዙር በዓለም አቀፍ ደረጃ በፕሮጀክቱ ለመታቀፍ ካመለከቱ 199 ፕሮጀክቶች መካከል የመጀመሪያ ዙር አፈፃፀማቸው ታይቶ ከተመረጡ 60 ፕሮጀክቶችች የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲው አንዱ ነው ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ ከ ጥር 01/2021 - ታኅሣሥ 31/2026 ዓ/ም የሚቆይ ሲሆን በ3ኛ ዲግሪ 6 ተማሪዎችንና በ2ኛ ዲግሪ 20 ተማሪዎችን ተቀብሎ በʻInfectious Diseaseʼ ማስተማር መጀመሩን የገለጹት አስተባባሪው 3ኛ ዲግሪ ያላቸውን 2 የ ʻPost Docʼ ተመራማሪዎችንም ለመደገፍ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ለተመራማሪዎች የገንዘብና የቁሳቁስ ወጪ የሚሸፍን ሲሆን ሴት ተመራማሪዎችንም ያበረታታል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት