በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ2013 ዓ/ም የ6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ላይ ውይይት ተካሄደ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ2013 ዓ/ም የ6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ጥር 25/2013 ዓ/ም ለካውንስል አባላት ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በዕቅድና በአፈፃፀም መካከል ያሉ ልዩነቶችን በማጥበብ፣ በመከለስና ውጤትን መሠረት በማድረግ ማከናወን ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ በተለይም ባለፉት 6 ወራት ጠንካራ አፈፃፀም ያሳዩ የሥራ ክፍሎችና ግለሰቦች ያላቸውን ቁርጠኝነትና ትጋት እንዲያስቀጥሉና በመማር ማስተማር፣ በምርምር፣ በቅድመና ድኅረ-ምረቃ መርሃ-ግብሮች የታዩ ለውጦች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ዶ/ር ዳምጠው አሳስበዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የስትራቴጂክ ዕ/ዝ/ት/ግ/ ዳይ/ዳይሬክተር አቶ አስፋው ደምሴ በበኩላቸው በጥናትና ምርምሮች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ-ምኅዳራዊ ችግሮችን በግንባር ቀደም በመለየት የኅብረተሰቡ ተጠቃሚነት እንዲጎለብትና ሴቶችን በአመራርነት፣ በመምህርነትና በምርምር ከማሳተፍ አንፃርም ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ፍትሐዊነትና ጥራት እንዲረጋገጥ በድኅረ-ምረቃ ትምህርት ተሳትፎና ተደራሽነት፣ በቅድመና ድኅረ-ምረቃ መርሃ-ግብሮች ጥራትና አግባብነትን ማሳደግ እንዲሁም ለሴት፣ ከታዳጊ ክልሎችና ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ካላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ለሚመጡና ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ልዩ እገዛ በማድረግ ረገድ ባለፉት 6 ወራት ዩኒቨርሲቲው በርካታ ሥራዎች መሥራቱን አቶ አስፋው ተናግረዋል፡፡

ጥራትን በማስቀደም ፈጠራን ማበረታታት እንዲሁም ቀልጣፋና ውጤታማ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት በመዘርጋት የተገልጋይ እርካታን ማሳደግ ያስፈልጋል ያሉት ዳይሬክተሩ አሳታፊ አስተዳደርና የዲሞክራሲ ባህል እንዲጎለብት ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ስትራቴጂያዊ መሠረቶችና መረጃዎች ከዩኒቨርሲቲው መሠረታዊ የመረጃ አደረጃጀትና አያያዝ አንፃር፣ የዩኒቨርሲቲው ራዕይ፣ ተልዕኮ፣ እሴቶችና መሪ ቃል፣ በ2013 ዓ/ም በተቃደው ዕቅድ መሠረት የምርምርና የልህቀት ማዕከላት ሚና፣ የመማር-ማስተማርና ዕድገት፣ የሀብት አጠቃቀም፣ የውስጥ አሠራር፣ የተማሪዎች፣ የመምህራንና የድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች መረጃ፣ ዕይታዎችና መግለጫዎች፣ የተገልጋይ እርካታ፣ በ6 ወራት የሥራ አፈፃፀም ላይ ያጋጠሙ ችግሮች፣ የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች እንዲሁም የትኩረት መስኮችና ውጤቶች በውይይቱ የተነሱ ነጥቦች ናቸው፡፡

በመማር-ማስተማር፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በማኅበረሰብ አግልግሎት ዘርፎች 1,825 መምህራን፣ 182 የቴክኒክና ድጋፊ ሰጪ ሠራተኞች፣ 4,892 የአስተዳደር ሠራተኞች በአጠቃላይ 6,899 ሠራተኞች በዩኒቨርሲቲው አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ሲሆን በቅድመና ድኅረ-ምረቃ መርሃ-ግብሮች 32,950 ተማሪዎች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ እንደቆዩ አቶ አስፋው ገልጸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት