አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከብራይት ፊውቸር አግሪካልቸር ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብና ከሌሎች የግብርና እና ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ለመጡ ባለሙያዎች የሴቶች ተሰጥዖ ልማት ላይ ያተኮረ ሥልጠና ከጥር 4/2013 ዓ/ም ጀምሮ ለ5 ቀናት ሰጥቷል፡፡

ሥራና ሕይወትን ማመጣጠን፣ የሥርዓተ-ፆታ መድልዖ፣ ሴቶች ወደ አመራር ለመምጣት የክሂሎት ማጣትና የተለያዩ ፕሮጀክቶችን መቅረጽ ሥልጠናው በዋናነት ያተኮረባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዝደንት ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን በመክፈቻ ንግግራቸው በሀገራችን የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ በተለያዩ የአመራር ደረጃዎችና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ የወደፊት ተስፋ ያላት፤ ‹‹እችላለሁ›› የምትል ሴት ለማፍራት መሰል ሥልጠናዎች ጠቀሜታቸው ከፍ ያለ ነው ብለዋል፡፡

የብራይት ፊውቸር አግሪካልቸር ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር ይስሐቅ ከቸሮ እንደተናገሩት ሥልጠናው በሴቶች ተሰጥዖ ልማትና በምግብ ዋስትና ሴቶችን ማብቃት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የምግብ ዋስትና ማስተማር፣ መመራመርና ማስተዳደርን የሚፈልግ በመሆኑ ለግብርና ሥራ አጋዥ የሆኑ አካላትን ማሠልጠን ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ወሳኝ ተግባር ነው፡፡ ያለ ሴቶች ተሳትፎ የምግብ ዋስትና ስለማይረጋገጥም የሴቶችን የተለያየ ተሰጥዖ ማሳደግ የለውጡ ጅማሬ ነው፡፡

የምርምርና ማ/አገ/ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በመዝጊያ ንግግራቸው የሀገርን እድገት ለማረጋገጥ ወሳኝ ከሆኑ መስኮች መካከል አንዱ የግብርና ሜካናይዜሽን መሆኑን ጠቅሰው ሥልጠናው ከምርምር አንፃር ዩኒቨርሲቲው በግብርናው መስክ ለቀረጸው ‹‹የተሻለ ተስፋ በግብርና›› ፕሮጀክት ባለሙያዎችን ሊረዳ የሚችል ግብዓት የሚገኝበት ነው ብለዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት ከሥልጠናው የሥርዓተ-ፆታ አመራርና የፕሮጀክት አቀራረጽና አስተዳደርን በተመለከተ ጥሩ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

በሥልጠናው መምህራን፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች፣ ዳይሬክተሮች፣ የሥርዓተ-ፆታ አስተባባሪዎች፣ ከፍተኛ ባለሙያዎችና የአስተዳደር ሠራተኞች ተሳትፈዋል፡፡