‹‹የባለድርሻ አካልት ጥምረት ለነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ መልሶ ማገገምና ዘላቂ ጥበቃ›› ጥር 21/2013 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ፓራዳይዝ ሎጅ የትብብርና የድርጊት የጋራ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ ጥምረቱ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን፣ ኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን፣ ቱሪዝም ኢትዮጵያ፣ የፌዴራል የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን፣ ግብርና ሚኒስቴር፣ የፌዴራል የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን፣ የደቡብና የኦሮሚያ ክልሎች የተለያዩ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች፣ GIZ Ethiopia፣ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም የግል ባለሀብቶችን ጨምሮ በአጠቃላይ 48 ባለድርሻ አካላትን ያቀፈ ነው፡፡ የባለድርሻ አካላቱን ጥምረት የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን በሊቀመንበርነት እንዲሁም ኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን በፀሐፊነት ይመራሉ፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ በፕሮግራሙ መግቢያ ባቀረቡት ሰነድ እንደተመለከተው ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ በአብዛኛው በሰው ሰራሽ ምክንያቶች ህልውናው ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ወድቋል፡፡ ልቅ ግጦሽ፣ የደን ጭፍጨፋ፣ ሕገ-ወጥ አደን፣ የዓባያና ጫሞ ሐይቆች በደለል መሞላትና በፓርኩ ክልል ውስጥ ሕገ-ወጥ ሰፈራ መስፋፋት ከምክንያቶቹ በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ስምምነቱ ለችግሮቹ በጋራ መፍትሔ በመስጠት ነጭ ሳር ፓርክን መልሶ እንዲያገግምና ዘላቂ ጥበቃ እንዲደረግለት ያለመ መሆኑ የቀድሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን መሥራች አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ተናግረዋል፡፡ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበትን ፓርክ ማዳን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት በመሆኑ ፋውንዴሽኑ ከባላድርሻ አካላቱ ጋር በመቀናጀት የሚጠበቅበትን ሁሉ ያከናውናል ብለዋል፡፡

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ እንደተናገሩት ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ለመሥራት መስማማታቸው ሕገ-ወጥ ሰፋሪዎችን ከፓርኩ ለማስወጣት፣ በፓርኩ ክልል ውስጥ ያለውን የሽፍታ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠርና ፓርኩን ለመታደግ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው ነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ በክልሉ ባለው አዋሳኝ ስፍራ ሕገ-ወጥ ሰፈራ ዋነኛ ችግር መሆኑን ጠቅሰው ሰፈራውን ተከትሎ ልቅ ግጦሽ፣ ከቤት እንስሳት ወደ ዱር እንስሳት የሚተላለፉ በሽታዎችና የብርቅዬ አራዊት ሞትና ሽሽት መበራከቱን እንዲሁም የኦነግ ሸኔ ሽፍቶች ፓርኩን እንደ መሸሸጊያ እየተጠቀሙበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፓርኩን ጨርሶ ከመጥፋት ለመታደግ በፓርኩ ክልል ለሰፈሩ ሰዎች አማራጭ የመኖሪያ ቦታና የገቢ ማስገኛ መፈለግ፣ ባህላዊ እሴቶችን ለፓርክ ጥበቃ ሥራ ማዋል፣ ፓርኩን ለመደበቂያ የሚጠቀሙበትን ሽፍቶች መቆጣጠርና ሕግ የማስከበር እርምጃዎችን መውሰድ ለመሳሰሉ ሥራዎች የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግና ከባለድርሻ አካላቱ ጋር በቅንጅት ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን አቶ አዲሱ ገልጸዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማ/አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ከዚህ ቀደም በነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ዙሪያ በተለይም ዓባያና ጫሞ ሐይቆችን በተመለከተ በዩኒቨርሲቲው በኩል በርካታ ጥናትና ምርምሮች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የባለድርሻ አካላት ጥምረት መፈጠሩና የስምምነት ፊርማ መከናወኑ በተናጠል ፓርኩን ለመታደግ የሚከናወኑ ተግባራትን የሚያጠናክርና የብዙሃኑን ትኩረት ለማግኘት የሚያስችል መሆኑን የተናገሩት ም/ፕሬዝደንቱ በቀጣይ በስምምነቱና በዝርዝር በሚወርዱ የሥራ ድርሻዎች መሠረት ዩኒቨርሲቲው የበኩሉን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡

ስምምነቱ ለሚቀጥሉት 5 ዓመታት የሚቆይ ሲሆን አማራጭ የአኗኗር ዘይቤ ጥናት፣ የሁለቱን ክልሎች የሥራ ኃላፊዎችንና ማኅበረሰቡን ማነቃቃትና ማሳመን፣ በፓርኩ ዙሪያ የተቀናጀ ማኅበረሰብ አቀፍ የአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ አማራጭ የኃይል ምንጮችን ማስተዋወቅ፣ ሕግ ማስከበር እና ሌሎችም ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት