ነፃ፣ ገለልተኛና ብቃት ያለው የአገልግሎት ዘርፍን በተቋማት ውስጥ ለማጠናከር የሚረዳ የአሠልጣኞች ሥልጠና በሰው ሀብት ልማትና አስተዳደር እና በተቋማዊ ለውጥ ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት ጥር 27/2013 ዓ.ም ለዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላት ተሰጥቷል፡፡

ነፃ፣ ገለልተኛና ብቃት ያለው የአገልግሎት ዘርፍ ግንባታ፣ የሰው ሀብት ልማትና ብቃት ማረጋገጫ ሥርዓት፣ የመንግሥት አገልግሎት እሴት ግንባታ እንዲሁም ሥነ-ምግባርና ጥራት ያለው የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ሥልጠናው በዋናነት ትኩረት ያደረገባቸው ነጥቦች ናቸው፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሰው ሀብት ልማትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ከአምላክነሽ ደሳለኝ እንደገለጹት ፍኖተ-ካርታው ነፃ፣ ገለልተኛና ብቃት ያለው እንዲሁም በመመሪያና ደንብ የሚመራ አገልግሎት ሰጪ ዘርፍ እንዲኖርና ከዚህ ቀደም ሲሠራበት የነበረውን በማሻሻል በተቋማት ውስጥ ውጤታማ አደረጃጀቶችን ለመፍጠር የሚረዳ ነው፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የመንግሥት ተቋም እንደመሆኑ ለለውጥ ግንባር ቀደም ሆኖ በመገኘት ከተገልጋዩ ፍላጎት ውጪ የሆኑ አሉታዊ አስተሳሰቦችን ማስቀረትና ለሁሉም ተደራሽ የሆነ ነፃና ገለልተኛ ተቋም መመሥረት የሚገባ መሆኑን ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል፡፡

የተቋማዊ ለውጥና የመልካም አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በኃይሉ በፍቃዱ በበኩላቸው የመንግሥት አገልግሎት ዘርፍ ለውጥ ፍኖተ-ካርታ በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት በሕዝብ የሚመረጥ መንግሥት የሚያወጣቸውን የልማት ዕቅዶች ማሳካት የሚችል፣ የሕዝብ አገልጋይነት መንፈስ የተላበሰ እና ነፃ፣ ገለልተኛና ብቃት ያለው የመንግሥት አገልግሎት ሥርዓት ለመገንባት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው በቀጥተኛው የሲቪል ሰርቪስ አሠራር ተመሥርቶ በመሥራትና ፖለቲካዊ አስተሳሰብን ከመንግሥት የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት መለየት ሲቻል መሆኑን አቶ በኃይሉ አስረድተዋል፡፡

ሥልጠናው በዋናነት የመንግሥት አገልግሎት ዘርፍ ከማንኛውም የፖለቲካ፣ የሃይማኖትና አካባቢያዊ አስተሳሰብ ወገንተኝነት የጸዳና ሁሉንም ዜጎች በእኩልነት ማስተዳደር በሚቻልበት መንገድ ላይና በአጠቃላይ ከ2013-2022 ዓ.ም ድረስ የአገልግሎት አሰጣጥ ዘርፉ ምን መምሰል እንዳለበት በስፋት ይዳስሳል፡፡

በሥልጠናው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት፣ ም/ፕሬዝደንቶች፣ ዳይሬክተሮች፣ የኮሌጅ ዲኖችና የሥራ ሂደት አስተባባሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት