አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀንን አከበረ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ110ኛ በሀገራችን ለ45ኛ ጊዜ የተከበረው ዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀን ‹‹የሴቶችን መብት የሚያከብር ማኅበረሰብ እንገንባ›› በሚል መሪ ቃል መጋቢት 8/2013 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው ተከብሯል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በመክፈቻ ንግግራቸው ሴቶች የኅብረተሰቡ ግማሽ አካል በመሆናቸው በአንድ ሀገር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጉልህ ሚና ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል፡፡ በተለያዩ ተፅዕኖዎች ምክንያት የሴቶች ተሳትፎ ከወንዶች ጋር ሲነፃፀር ያነሰ ነው ያሉት ፕሬዝደንቱ አሁን በደረስንበት የዕድገት ደረጃ በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገራችን በሁሉም መስኮች የሴቶች ተሳትፎ በመጠንና በውጤታማነት ትልቅ ዕድገት እያሳየ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲውን ለሴት ተማሪዎች ምቹ ለማድረግ ሁሉም በትብብር መሥራት እንደሚጠበቅበትም ፕሬዝደንቱ አሳስበዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በዓለም፣ በሀገርና በተቋም ደረጃ የሴቶችን ስኬት በጋራ ዕውቅና መስጠትና የሴቶችን እኩልነት፣ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በዓሉ በየዓመቱ የሚከበርበት ዓላማ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህሌ ገልጸዋል፡፡ በዓለማችን ቀጣይነት ያለው ዕድገት እንዲኖር ከታሰበ ሴቶችና ወንዶች በሁሉም መስክ እኩል ተሳታፊ መሆን እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡

በበዓሉ በሥርዓተ-ፆታ እሳቤ ዙሪያ ግንዛቤ ለማዳበር የሚያስችሉ የመወያያ ርዕሶች ቀርበው በታዳሚዎች ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን በቤልጂዬም ሀገር የ3ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙት መምህርት ትዝታ እንዳለ እና የቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዝደንት ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን የሕይወት ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡ በማጠቃለያውም በ2012 የትምህርት ዘመን 1ኛ ሴሚስተር ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ሴት ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ሴት ሠራተኞችና ተማሪዎች በበዓሉ ላይ ተሳትፈዋል፡፡