አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና የጋሞ ዞን አስተዳደር በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና የጋሞ ዞን አስተዳደር በምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፎች ላይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የትብብር መግባቢያ ስምምነት መጋቢት 21/2013 ዓ/ም ተፈራርመዋል፡፡

በመግባቢያ ስምምነቱ ዞኑና ዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰቡን ሕይወት በዘላቂነት መቀየር በሚያስችሉ የምርምር፣ የማኅበረሰብ አገልግሎት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የአቅም ግንባታ ዘርፎች ላይ በጋራ እንደሚሠሩ ተቀምጧል፡፡ ስምምነቱ ለ4 ዓመታት የሚቆይ ሲሆን ሁለቱ አካላት የሰው ሀብት፣ ቁሳቁስና ፋይናንስ በጋራ እንደሚጠቀሙ በስምምነቱ ተጠቅሷል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባለሙያዎችን በማፍራት፣ ችግር ፈቺ ምርምሮችን በማካሄድና ቴክኖሎጂዎችን በማላመድና በማሸጋገር ለሀገሪቱ ዕድገት እንዲሠሩና ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ኃላፊነት የተጣለባቸው መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ አንፃር አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን ከጋሞ ዞን አስተዳደር ጋር በቅንጅት ለመሥራት መስማማቱ የዞኑን ሕዝብ ተጠቃሚነት ከፍ ከማድረጉ ባሻገር ዩኒቨርሲቲው የተጣለበትን ሀገራዊ ተልዕኮና ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ የሚያግዘው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የጋሞ ዞን ም/ዋና አስተዳዳሪና የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ ም/ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የጋሞ ዞንና የአርባ ምንጭ ከተማ መገለጫ መሆኑን ጠቅሰው በተለይ ዩኒቨርሲቲው በቅርቡ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ተብሎ መለየቱ ለዞናችን የሚያስገኘው ጠቀሜታ ጉልህ ነው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በሰው ኃይል ልማት እና በምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ለዞኑ ማኅበረሰብና መንግሥት ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክቷል ያሉት አስተዳዳሪው የመግባቢያ ስምምነቱ ትብብርና ግንኙነታችንን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የማኅበረሰባችንን ዘረፈ ብዙ ችግሮች ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የማይተካ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ዩኒቨርሲቲው በጋሞ ዞን እና በሌሎች ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በርካታ የምርምር፣ የማኅበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸው የመግባቢያ ስምምነቱ ዩኒቨርሲቲው የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት እንዲወጣና ውጤታማ የምርምር ሥራዎችን ለመሥራት ያግዛል ብለዋል፡፡

በዕለቱ በተደረገው ውይይትም ዩኒቨርሲቲው እያከናወናቸው የሚገኙ ዘረፈ ብዙ ተግባራት የተመሰገኑ ሲሆን ተጀምረው ወደ ተግባር ያልተቀየሩ እንደ ኩልፎ ተፋሰስ ልማትና ሰልባጅ ተራ አደባባይ ፕሮጀክቶች ወደ ተግባር እንዲቀየሩ፣ አርባ ምንጭ ከተማን ማዕከል ያደረጉ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው እንዲሠሩ፣ በማዕድን ፍለጋ ላይ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ፣ በግብርናው ዘርፍ የሚስተዋሉ የበሽታና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲሠራ እንዲሁም በየዘርፉ የሚስተዋሉ የሰው ኃይል አቅም ውስንነቶችን ለመቅረፍ የአቅም ግንባታ ሥራዎች በስፋት እንዲሠሩ አስተያየት ተሰጥቷል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት