የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ከየካቲት 30 - መጋቢት 2/2013 ዓ/ም ሥልጠናዊ ውይይት አካሂዷል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በማድረግ ስለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከምሥረታው ጀምሮ አሁን እስካለበት የምርምር ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ድረስ ያለውን አጠቃላይ ሂደት ገለጻ አድርገዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የአስተዳደርና መሠረተ ልማት ዳይሬክተር ጄኔራል ዶ/ር ሰለሞን አብርሃ ሥልጠናው በዋናነት የሪፎርም ሥራዎችን ወደ መሬት በማውረድ በፖሊሲዎች፣ በስትራቴጂዎች፣ በፕሮግራሞችና በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አጠቃላይ ሀገራዊ የክሂሎት ግንዛቤ በመፍጠር የአመራሩን አቅም ለመገንባት የተጀመረ ዕቅድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተልዕኮ የሳይንስ ባህልና ሳይንሳዊ አሠራሮች እንዲጎለብቱ ማድረግ እንዲሁም ከከፍተኛ ትምህርት ጋር በተያያዘ በዕውቀት፣ በክሂሎትና በመልካም ሥነ-ምግባር የታነፀ፣ የሀገር ፍቅር ያለውና የሠለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ በምርምር ዘርፍም ችግር ፈቺ ጥናቶችን በማካሄድ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅና በማሸጋገር ሀገራችን ለያዘችው የብልፅግና ጉዞ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ይፈለጋል ብለዋል፡፡

ዶ/ር ሰለሞን በተጨማሪም በየተቋማቱ የሚታዩትን የአመራር ስምሪት ክፍተቶች ለመቅረፍና በተቋማት ውስጥ ወጥ የሆነ አሠራር እንዲሰፍን ለማስቻል ውይይቶችን ማከናወን አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ሰለሞን ከዚህም ዓላማና ተልዕኮ አንጻር የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተለያዩ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችንና ፕሮግራሞችን ነድፎ እየሠራ ነው፡፡ በቀጣይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአመራርነት ዕውቀትና ክሂሎት በሠለጠኑ አመራሮች እንዲመሩ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ዶ/ር ሰለሞን ተናግረዋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በቀጣይ 10 ዓመታት ሀገራዊ የልማት፣ የዕድገትና የብልፅግና ጉዞ ስኬታማ እንዲሆን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ተልዕኮ ወስዶ እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡ እነዚህ ተልዕኮዎች ከዩኒቨርሲቲዎቻችን ጋር ተዋህደውና ተሰናስለው በቀጣይ 10 ዓመታት ሀገራዊው የሪፎርም ጉዞ እንዲሳካ የኢፌዴሪ ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችን፣ ፕሮግራሞችን፣ የ10 ዓመት መሪ ዕቅዶችንና የ5 ዓመት የመካከለኛ ዘመን ዕቅዶችን አዘጋጅቶ ከተቋማት አመራሮች ጋር ውይይት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ በዚህም ሥልጠናዊ ውይይት ትልቁን ሀገራዊ ግብ ለማሳካት ዩኒቨርሲቲዎች ከሴክተር መሥሪያ ቤቱ በወሰዱት የፖሊሲና የፕሮግራሞች አንኳር ጉዳዮች ላይ በመወያየት፣ በመግባባትና ፖሊሲዎቹን አሟልቶ የጋራ በማድረግ ወደ ሥራ እንዲገባ አቅም ለመገንባት ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ፕሮፌሰር አፈወርቅ እንደተናገሩት የትምህርት ጥራትን ዕውን ለማድረግ ትልቁ ሀገራዊ ሥራ በዕውቀትና የሙያ ሥነ-ምግባር የታነጹ፣ ብቁና በቂ ምሁራንን ለኢንደስትሪው ማዘጋጀት ሲሆን ጥራትን ለማስጠበቅ ቁልፍ ጉዳይ የአመራርን አቅም መገንባት ነው፡፡ በዕውቀት ላይ ተመስርተው የሚመሩትንና የሚሠሩትን በደንብ ጠንቅቀው የሚገነዘቡ አመራሮችን ከማፍራት አንፃር ሥልጠናዊ ውይይቱ ወሳኝ እንደሆነና የዚህም ድምር ውጤት ለትምህርት ጥራቱ ማደግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ውስጥ ከዚህ ቀደም ያላከወኗቸውን ጉዳዮች ጎን ለጎን በማሳካት የጥራትና አግባብነት እንዲሁም የፍትሃዊ ተደራሽነት ጉዳዮችን ለመመለስ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመሆን የኢፌዴሪ ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተቋሞችን አቅም ገንብቶ ውጤታማ ለማድረግ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ በመጨረሻም የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻዎች የሚጠበቅባቸውን ግዴታ እንዲወጡ አመራሩ በትኩረት እንዲሠራ አሳስበዋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ ፕሮፌሰር ያለው እንዳወቅ እንደገለጹት ፖሊሲ አቅጣጫ አመላካች እንደመሆኑ መጠን ይህንን አቅጣጫ መሠረት አድርገን እያንዳንዳችን የተሰጠንን ኃላፊነት ልናከናውን ይገባል፡፡ ተቋማትን በምንመራበት ጊዜ ትልቁ ሚና ሊሆን የሚገባው የተቋሙን ፖሊሲ በማወቅ በአሠራሩ መሠረት ማከናወን መቻል ነው ብለዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ፖሊሲና ስትራቴጂው በቀጣይ የከፍተኛ ትምህርት ሂደትን የሚወስን ስለሆነ እያንዳንዳችን አንብበንና ግንዛቤያችንን አጎልብተን ሥራችንን በአግባቡ ማከናወን እንደሚገባ እንዲሁም በፖሊሲው ላይ የምንሰጠው ግብዓትም ትልቅ ዋጋ እንደሚኖረው ፕሮፌሰር ያለው ተናግረዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የፖሊሲውን አስፈላጊነት፣ አተገባበርና ግምገማ እንዲሁም ተደራሽ ከማድረግ አንጻርና ለፖሊሲው መቀረጽ ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

በሥልጠናው የፕሮግራም ሰነዶች፣ የከፍተኛ ትምህርት የ10 ዓመታት ፍኖተ ካርታ፣ የሳይንስ ፖሊሲና ስትራቴጂ፣ የሳይንስ ንዑስ ዘርፍ የ10 ዓመታት ፍኖተ ካርታ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ቅበላና ምደባ ፖሊሲ፣ የተቋማት አቅም ግንባታ ቁልፍ ተግባር አፈጻጸም እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ቁልፍ ተግባር አፈጻጸም አመላካቾችን አስመልክቶ ሰፊ ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

የሥልጠናው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች ተመሳሳይ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ፖሊሲውን አንብበው ማነቆ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በመወያየት በቀጣይ የፖሊሲ ክለሳ በሚደረግበት ወቅት መሠረታዊ የሆኑና ሳይካተቱ የቀሩ ጉዳዮችን የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንደ ግብዓት እንዲወስድ የሚረዳ ከመሆኑም ባሻገር አመራሩ ከፖሊሲው ጋር ይበልጥ ትውውቅ እንዲኖረውና በቀጣይ ሥራዎች የሚሠሩበትን አግባብ ያሳየ ነው ብለዋል፡፡ ሥልጠናው እያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ እንደ ተቋም አሁን ባለበት አቋም ላይ ምን መጨመር እንዳለበት ዕይታ ያሰፋና ለፖሊሲው ትውውቅም ከፍተኛ አቅም የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚሁ መልክ የተያዘውን ግንዛቤ ለየዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በማውረድ ትስስሩን የበለጠ ለማጠናከርና ፖሊሲዎቹን በየደረጃው ለማስተዋወቅ ኃላፊነት የተቀበልንበት ነውም ብለዋል፡፡

በፕሮግራሙ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዳይሬክተር ጄኔራሎችና ከፍተኛ አማካሪዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ዳይሬክተሮች፣ የከፍተኛ ትምህርት ስትራቴጂ ማዕከል ዳይሬክተሮች፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንቶች፣ ምክትል ፕሬዝደንቶች ሳይንቲፊክ ዳይሬክተሮችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት