በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመው STEM ማዕከል ተመረቀ

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመው STEM ማዕከል /Science, Technology, Engineering & Math Center/ መጋቢት 22/2013 ዓ/ም ተመርቋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከ STEM ፕሮጀክት ጋር የመግባቢያ ውል ስምምነት ተፈራርሟል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው የ STEM ጉዳይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያደገና ትኩረትን እያገኘ መምጣቱን ገልጸው መጪው ትውልድ የሳይንስን ምንነት በመገንዘብ በSTEM ፕሮጀክት ዘርፎች ዕውቀቱን አበልጽጎና አደራጅቶ ለመምራት ይችል ዘንድ ፕሮጀክቱ ዓይነተኛ መሳሪያ ነው ብለዋል፡፡ ታዳጊዎችን በሳይንስ ኮትኩቶ ማሳደግ በሀገራችንም ሆነ በዓለም መድረክ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ እጅግ መሠረታዊ ነገር መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ STEM ፕሮጀክት ሰንቆ የተነሳው ዓላማ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ በቀጣይ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ተቋም ልዩ ተሰጥኦ ባላቸው ተማሪዎች ላይ በመሥራት የወደፊት ተመራማሪዎችና ሊቃውንት እንዲፈሩ አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የዩኒቨርሲቲው STEM ማዕከል ኃላፊ ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ዩኒቨርሲቲው ከ2008 ዓ/ም ጀምሮ በአጠቃላይ ትምህርት ጥሩ አፈጻጸም ያላቸው ከ7ኛ-12ኛ ክፍል ያሉ 350 ተማሪዎች በክረምት ለ 45 ቀናት በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ቆይተው የተለያዩ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ዕውቀቶችን እንዲቀስሙ ያደረገ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ዝንባሌ ያላቸው ተማሪዎች ቴክኖሎጂውን እየተጠቀሙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ማዕከሉ በተለያዩ የቤተ-ሙከራ ግብዓቶች ተደራጅቶ መቋቋሙ ፕሮግራሙን አጠናክረን እንድንሠራ ይጠቅማል ያሉት ዶ/ር ተክሉ በቀጣይ የመዋቅር ለውጦችን በማድረግና ማዕከሉን በሰው ኃይልም ሆነ በግብዓት በማደራጀት አገልግሎቱ ሳይቋረጥ እንዲሰጥ ይደረጋል ብለዋል፡፡ ቴክኖሎጂውን ወደ ገጠር ለማዳረስ ያመች ዘንድ ተንቀሳቃሽ ቤተ-ሙከራዎችን ተደራሽ ለማድረግ ዕቅድ መያዙንም ጠቁመዋል፡፡

የ STEM ፕሮጀክት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ቅድስት ገ/አምላክ በበኩላቸው ማዕከሉ ተማሪዎች በክፍል ውስጥ የሚማሩትን በተግባር እንዲሞክሩና ወደ ፈጠራ ሥራ እንዲቀይሩ እንዲሁም በየትኛው ዘርፍ የተሻለ ዕውቀት እንዳላቸው እንዲለዩ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የፈጠራ ሥራውን አሻሽለው በመሥራትና ወደ ገንዘብ በመቀየር የኢኮኖሚ እድገት በማምጣት ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውን፣ ማኅበረሰቡንና ሀገርን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ዕድል ያመቻቻልም ብለዋል፡፡

እንደ ወ/ሮ ቅድስት ገለጻ ማዕከሉ በ48 ዩኒቨርሲቲዎች የተከፈተ ቢሆንም ተጠናክሮ እየሠራ የሚገኘው በጥቂት ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተጠቃሽ ነው፡፡ ለማዕከሉ የሚያስፈልጉ ወጪዎችን በመሸፈን፣ ሥልጠና በማዘጋጀት፣ የቤተ-ሙከራ ቁሳቁሶችን በማሟላት እንዲሁም አዳዲስ ፐሮግራሞችን በመቅረጽና ሌሎች ሥራዎችን በጋራ በመሥራት ለ2 ዓመታት ከዩኒቨርሲቲው ጋር እንደሚቆዩም ተናግረዋል፡፡

የማዕከሉ ተጠቃሚ ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት ማዕከሉ በተለያየ ዘርፍ ተሰጥኦ ያላቸውና ዕድሉን ያላገኙ ተማሪዎች ችሎታቸውን አውጥተው ተግባራዊ ሊያደርጉ የሚችሉበትንና ዕውቀት የሚያገኙበትን ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል፡፡

በሥነ-ሥርዓቱም የ STEM Power ዋና ዳይሬክተር፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና ዳይሬክተሮች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው STEM ማዕከል አስተባባሪዎችና መምህራን የተገኙ ሲሆን በሥነ-ሥርዓቱ ፍፃሜ የማዕከሉ ቤተ-ሙከራዎች ጉብኝት ተካሂዷል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት