ዩኒቨርሲቲው ከጋሞ ዞን ሰላምና ፀጥታ ግንባታ መምሪያ ጋር በመተባበር ‹‹ሁሉ አቀፍ የማኅበረሰብ ተሳትፎ ለዘላቂ ሰላም›› በሚል መሪ ቃል በቁጫ ወረዳ ሰላም በር ከተማ የካቲት 24/2013 ዓ.ም የመጀመሪያ ዙር ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

ሥልጠናው ‹‹ሁሉ አቀፍ ማኅበረሰብ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ›› እና ‹‹በሃይማኖቶች መካከል መቻቻልና መከባበር›› በሚሉ ይዘቶች ዙሪያ መሰጠቱን የጋሞ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ የግጭት ዘላቂ መፍትሄ ሥራ ትግበራ ከፍተኛ ባለሙያና አሠልጣኝ አቶ መሰለ እንግዳ ተናግረዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ከተሰጡት ተልዕኮዎች አንዱ ማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ሲሆን ሥራዎቹም ከማኅበረሰቡ ጋር በጋራ የሚሠሩ ናቸው ብለዋል፡፡ የማኅበረሰብ አገልግሎት በማኅበረሰቡ መካከል መግባባት፣ ትስስር፣ አንድነትና ኅብረትን በመፍጠር እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ ምርምሮችን በማካሄድ፣ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ግኝቶችን በማቅረብና ሥልጠናዎችን በመስጠት እንደሚከናወን ተ/ፕ በኃይሉ አስረድተዋል፡፡

የጋሞ ዞን ሰላምና ፀጥታ ግንባታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሞናዬ ሞሰሌ ሰላም ለሰው ልጆች መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከሚጠቀሱት ሁሉ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ተናግረው በሰላም ዙሪያ ማኅበረሰቡ መመካከሩና መግባባቱ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ ዜጎች ሰላም በሰፈነበት ዓውድ ውስጥ ሲኖሩ ማኅበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ለማከናወን ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ያሉት አቶ ሞናዬ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በተሟላ ሁኔታ ሲረጋገጡ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለው መተማመን የሚጎለብት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሥልጠናው ከቁጫ በመቀጠል በካምባና ጨንቻ ወረዳዎች የሚሰጥ ሲሆን የማጠቃለያ ፕሮግራሙ በአርባ ምንጭ ከተማ እንደሚከናወን የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት፣ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ የጋሞ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ፣ የጋሞ ዞን ሰላምና ፀጥታ ግንባታ መምሪያ ኃላፊ፣ የጋሞ ዞን ሚሊሻ ጽ/ቤት ኃላፊ፣ የሰላም በር ከተማ ከንቲባ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የጋሞ አባቶች፣ ወጣቶችና በአቅራቢያ ካሉ ቀበሌዎች የተጋበዙ ተሳታፊዎች በፕሮግራሙ ተገኝተዋል፡፡