በኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴርና በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አዘጋጅነት 9ኛው ‹‹የሕክምና ት/ቤቶች ካውንስል በኢትዮጵያ›› ጉባዔ ከመጋቢት 16-17/2013 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ፓራዳይዝ ሎጅ አካሂዷል፡፡   ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በጉባዔው በ2012 ዓ/ም በአዳማ የተካሄደው 8ኛው ስብሰባ ፍሬ ሃሳቦች በአጭሩ የቀረቡ ሲሆን የሕክምና ትምህርትና አገልግሎት ጥራት፣ የታዩ መሻሻሎችና ተግዳሮቶች፣ የሙያ ማሻሻያና የሙያ ፈቃድ ፈተና አሰጣጥ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም በሕክምና ትምህርቶች፣ የስፔሻሊቲና የሰብ ስፔሻሊቲ ፍኖተ ካርታ፣ የሕክምና ት/ቤቶች ዕውቅና አሰጣጥ፣ አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት ሥራ ላይ ማዋል እንዲሁም በዩኒቨርሲቲ ሥር የሚገኙ ሆስፒታሎች መንግሥታዊ መዋቅር ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በእንኳን ደኅና መጣችሁ ንግግራቸው ካውንስሉ 9ኛ ጉባዔውን በዩኒቨርሲቲው በማካሄዱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው መሰል ጉባዔዎች የተለያዩ ልምድና ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ፣ በጋራ ለማቀድና የራስን ድርሻ ወስዶ በኃላፊነት ለመሥራት ከፍተኛ ሚና ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሕክምና ትምህርት አሰጣጥ ጥራትን በመጨመር፣ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርትና ሥልጠና በመስጠትና ብቁ ባለሙያ በማፍራት የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሳደግ ‹‹የሕክምና ት/ቤቶች ካውንስል በኢትዮጵያ›› መቋቋሙን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ት/ቤት ዲንና የካውንስሉ ፕሬዝደንት ዶ/ር ተቋም ደበበ ገልጸዋል፡፡ ካውንስሉ ከዚህ ቀደም ባደረጋቸው ውይይቶች በሕክምና ዘርፍ ሥርዓተ ትምህርትን ማሻሻል በሚቻልበት መንገድና በሚያጋጥሙ ችግሮች ላይ በመነጋገር በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሻሻለ ሥርዓተ ትምህርት እንዲቀረጽ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር የሰው ሀብት ልማት ዳይሬክቶሬት አማካሪ ፕሮፌሰር አብርሃም ኃ/አምላክ በበኩላቸው ጉባዔው 40 የሚሆኑ የካውንስሉ አባል የሕክምና ት/ቤቶች የሚሳተፉበትና የሀገራችንን የሕክምና ትምህርት ማሳደግ በተለይም በማስተማሪያ ሆስፒታሎች ውስጥ የሚሰጠውን የሕክምና አገልግሎት ማሻሻል በሚቻልበት መንገድ ላይ የሚመክር ነው ብለዋል፡፡ የተለያዩ የሕክምና ት/ቤቶች በሥራቸው ሆስፒታሎችን የሚያስተዳድሩ በመሆኑ የሚገጥሟቸውን ችግሮች የልምድ ልውውጥ ለማድረግና መፍትሔ ለማፈላለግ የሚረዳ መድረክ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

እንደ ፕሮፌሰር አብርሃም ገለጻ ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ የሕክምና ተቋማትን በአስፈላጊ ግብዓቶች ከማደራጀት ባሻገር የሕክምና ባለሙያዎችን በጥራት ማፍራት የሚያስፈልግ በመሆኑ ጤና ሚኒስቴር ባለው አቅም ሁሉ በመማር ማስተማር ሂደት እገዛዎችን የሚያደርግ ሲሆን ባለፉት ስድስት ዓመታት በማስተማሪያ ት/ቤቶች በገንዘብ ሲተመን 10 ቢሊየን ብር የሚያወጡ የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ እንዲሁም የክሂሎት ማዕከላት ማደራጀትና የመምህራን ሥልጠናዎችን በትብብር አከናውኗል፡፡

‹‹የሕክምና ት/ቤቶች ካውንስል በኢትዮጵያ›› ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በሕክምና ትምህርትና አገልግሎት ጥራት ላይ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ ተናግረዋል፡፡ ከሥራዎቹም መካከል በሀገሪቱ የሚገኙ የሕክምና ትምህርት ቤቶች የሚጠቀሟቸውን የተለያዩ ሥርዓተ ትምህርቶች ወደ አንድ ለማምጣት የሥርዓተ ትምህርት ቀረጻ መከናወኑ ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ጥቂት ዩኒቨርሲቲዎች በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መሠረት ወደ ሥራ መግባታቸውን የተናገሩት ዶ/ር ታምሩ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ት/ቤት ከ2013 የትምህርት ዘመን 2ኛ አጋማሽ ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡ የውይይት መድረኩ በሕክምናው ዘርፍ በተለይም በትምህርትና አገልግሎት ጥራት ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በዝርዝር

በመወያየት ብቃት ያላቸው የሕክምና ባለሙያዎችን ለማፍራትና ኅብረተሰቡን በተሻለ መልኩ ለማገልገል የሚረዳ መሆኑን ዶ/ር ታምሩ ገልጸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት