የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኅብረት የ2013 ዓ.ም የመጀመሪያ ዙር የፓርላማ ስብሰባውን ‹‹ሰላማዊና ምቹ የመማር ማስተማሪ ሂደት እንዲኖር ኅብረታችን ትልቁን ሚና ይጫወታል›› በሚል መሪ ቃል መጋቢት 19/2013 ዓ.ም አካሂዷል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በመክፈቻ ንግግራቸው በ2012 ዓ.ም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ተቋርጦ መቆየቱን አስታውሰው 2013 የትምህርት ዘመን ስኬታማ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማስቀጠል ሁሉም በየደረጃው ተገቢውን ጥንቃቄ እያደረገ የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል፡፡

የመማር ማስተማር ሂደት ችግሮች፣ የ2012 ዓ.ም የሥራ አፈፃፀም ሪፖርትና የ2013 ዓ.ም ዕቅድ፣ የፓርላማ ዋና እና ምክትል አፈ-ጉባዔዎችን መምረጥ እንዲሁም የኅብረቱን መተዳደሪያ ደንብ ማጽደቅ በስብሰባው የተነሱ አጀንዳዎች መሆናቸውን የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝደንት ተማሪ አንዳርጋቸው ደስታ ተናግሯል፡፡

የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር መልካሙ ማዳ በመማር ማስተማር፣ በአስተዳደርና በተማሪ አገልግሎት ዘርፍ በተነሱት ጥያቄዎች መሠረት በቀጣይ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ቃል ገብተው ተማሪዎች ራሳቸውን ከኮሮና ወረርሽኝ እንዲጠብቁ አሳስበዋል፡፡

የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አየልኝ ጎታ የተማሪ ፓርላማ ስብሰባ ለተማሪውም ሆነ ለዩኒቨርሲቲው ትልቅ ግብዓት መሆኑን ጠቅሰው በመማር ማስተማርና በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የዩኒቨርሲቲው አመራርና የተማሪ ኅብረት በቅርበት እንዲሠራ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

የልዩ ፍላጎት ተማሪና የጫሞ ካምፓስ የተማሪ ኅብረት ተወካይ የሆነችው ተማሪ አትክልት ቢሰጥ የፓርላማው ሪፖርት አቀራረብና ሃሳቧን በነፃነት ለመስጠት ዕድል ማግኘቷ እንዳስደሰታት ገልጻለች፡፡

በስብስባው መጨረሻ በተደረገው የፓርላማ አፈ-ጉባዔ ምርጫ ተማሪ ተመስገን አዲሱ ዋና አፈ-ጉባዔና ተማሪ አንሙት ጎዴ ም/አፈ-ጉባዔ ሆነው የተመረጡ ሲሆን የተማሪ ኅብረት ፓርላማ መተዳደሪያ ደንብም ቀርቦ ጸድቋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት