በዩኒቨርሲቲው የግብርና ሣይንስ ኮሌጅ በስሩ በተከፈቱ 7 የትምህርት መስኮች ዘርፈ ብዙ የምርምር ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በእንስሳት፣ በእፅዋት እና ደን ሳይንስ የትምህት ዘርፎች የሚካሄዱት ምርምሮች ለአብነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የዕፅዋት ሣይንስ ትምህርት ክፍል ተጠሪ አቶ ኪያ አደሬ እንደገለጹት በትምህርት ክፍላቸው ጥራጥሬና ሰብሎችን አራርቆ መዝራት፣ ተፈጥሯዊና ዘመናዊ ማዳበሪያ አጠቃቀምን ጨምሮ የተለያየ እንክብካቤ በመስጠት የምርታማነት ዕድገትን ለመጨመር የሚያስችሉ ዘዴዎችን ለመለየት በትጋት እየተሰራ ነው፡፡

በዋናው ግቢ የእርሻ ምርምር ማሳያ ላይ እየተካሄደ ያለውን የሸንኮራ አገዳ ምርምር አስመልክተው ፕሮፌሰር አብዱል ቀይም ከሃን እንደተናገሩት ዩ ኤስ ኤን ጨምሮ ከተለያዩ 8 አገሮች የተሰባሰቡ 16 ዓይነት የሸንኮራ አገዳ ምርጥ ዝርያዎች እየተጠኑ ነው፡፡ ለወደፊትም ለኦሞ ኩራዝ፣ ለወንጂና ለመተሐራ ስኳር ፋብሪካዎች የተሻለ ግብዓት እንዲሆን ምርምሩን ስኬታማ ለማድረግ ከኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ጋር በቅንጅት እየሠሩ መሆናቸውን ፕሮፌሰሩ ገልፀዋል፡፡

የደን ሣይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ዮናስ ኡጎ በበኩላቸው ትምህርት ክፍላቸው የአካባቢውን የደን ሀብት ለማሳደግ የሚያስችሉና ከአካባቢው የአየር ንብረት ጋር ተዛማጅ የሚሆኑ የዛፍ ዝርያዎችን በማጥናት ችግኝ አፍልቶ ለዩኒቨርሲቲው ካምፓሶችና ለአካባቢው ማኅበረሰብ የማድረስ ሥራ መጀመሩን ገልፀዋል፡፡ በዚህ ዓመት ከድሬዳዋ ተገዝቶ የመጣውን የእውነተኛ ኒም ዛፍ ችግኝ በማፍላት እስከ አሁን ከ14,000 በላይ ችግኞች የተሰራጩ ሲሆን በዘርፉ ቀጣይ ምርምሮችን በማካሄድ ከአንድ በላይ ጥቅም ሊሰጡ የሚችሉ ዛፎችን ለማስተዋወቅና ለማላመድ አቅደን እየሠራን ነው ብለዋል፡፡

የእንስሳት ሣይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ሠይፉ ብርሃኑ በትምህርት ክፍላቸው ምርጥ የወተት ላም ዝርያዎችን ከአካባቢው ዝርያዎች ጋር የማዳቀል ሥራ በቅርቡ የሚጀመር መሆኑን በመጥቀስ የእንስሳት መኖ ዕፅዋትን በማላመድ ለምርጥ የወተት ላሞችና ለዶሮ እርባታ ሥራዎች ግብዓት እንዲሆኑ ይደረጋል ብለዋል፡፡ የፕሮፌሰር ሰለሞን ‘chicken brooding box’ የተባለ ዘመናዊ የጫጩት ማሳደጊያ አጠቃቀም ጥናት እንደተጠናቀቀም ቴክኖሎጂው ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ይሆናል፡፡

የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ነጂብ መሐመድ እንደተናገሩት ኮሌጁ ከተቋቋመ ገና ሁለት ዓመት ብቻ ቢሆነውም እየሠራቸው ያሉት ተግባራት ተስፋ ሰጪ ናቸው፡፡ ዲኑ በኮሌጁ ባሉት ሁሉም የትምህርት ክፍሎች በመምህራንና በተለይም በተመራቂ ተማሪዎች አበረታች ምርምሮች በመካሄድ ላይ መሆናቸውን ገልፀው የተጀመሩትና ሌሎችም አዳዲስ ምርምሮች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡