በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ በስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ‹‹የስፖርት ህክምናና ኦርቶፔዲክ ሰርጀሪ›› የሚባል ፕሮግራም በማስትሬት ድግሪ ደረጃ ተቀርፆ ግንቦት 25/2007 /ም የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት፣ የዘርፉ ምሁራንና ሌሎችም በተገኙበት የስርዓተ -ትምህርት ግምገማ ተደርጓል ፡፡

በሀገራችን የአትሌቲክስ ስፖርት በላቀ ደረጃ እንዲያድግ በስፖርት ህክምናና በኦርቶፔዲክ ሰርጀሪ የሰለጠነ ባለሙያ ማፍራት የጎላ ሚና ይጫወታል ፡፡ይህንን በመረዳት የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ በተለይም የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል በመስኩ ማስትሬት ድግሪ ስርዓተ-ትምህርት ቀርፆ ባለሙያዎችን ለማፍራት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ የኮሌጁ ዲን ዶ/ር አለማየሁ ኃ/ሚካኤል ገልፀዋል ፡፡

በዩኒቨርሲቲው የስፖርት ሣይንስ መምህር ዶ/ር ሞላ ዶዮ የትምህርት ክፍሉን መከፈትና ዓላማውን አስመልክተው በሰጡት ገለፃ መንግስት በቀየሰው ፖሊሲ መሠረት የስፖርተኛውን የመስራት አቅም ለማጎልበት፣ የአመጋገብ ስርአትን ለማስተካከል እንዲሁም የስፖርት እንቅስቃሴ በሚደረግበት ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን በማቃለል በሀገር አቀፍና በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ተፎካካሪ የሆኑ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚያስችል ነው ብለዋል ፡፡

ኦርቶፔዲክ ሰርጀሪን በዩኒቨርሲቲው ደረጃ ባለው የሰው ኃይልና ለትምህርቱ ከሚያስፈልጉ ግብዓቶች አንፃር ለጊዜው ማስቀጠል ባይቻልም ከህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ጋር በጋራ በመሆን የስፖርት ህክምናውን ብቻ በ2008 /ም ለመጀመር መስማማታቸውን ዶ/ር ሞላ ገልፀዋል ፡፡ በስርዓተ ትምህርቱ ቀረፃ ከፍተኛ ድርሻ የነበራቸው ዶ/ር ሞላ አያይዘውም የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ለስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍሉ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በማደራጀት ላደረገው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል፡፡