በዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የመጀመሪያው ‹‹የምህንድስና እና የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችና ተግዳሮቶች ለዘላቂ ልማት›› አውደ ጥናት ተካሄደ
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ‹‹የምህንድስና እና የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችና ተግዳሮቶች ለዘላቂ ልማት›› በሚል ረዕስ አገራዊ ዓውድ- ጥናት ከሚያዚያ 4-5/2011 ዓ/ም ለመጀመሪያ ጊዜ አካሄዷል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት በአሁኑ ወቅት የፈጠራና የምርምር ውጤቶችን ለተጠቃሚው ከማድረስ አንፃር አጠቃላይ ከሀገራዊ ፍላጎት ጋር ሲነፃፀር  ውስንነት እንዳለበት ጠቁመው ይህን ለማሻሻል ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት ወጥነት ያለው ተቋማዊ አደረጃጀትና የፖሊሲ አቅጣጫዎችን በመከተል የሚሰሩ ከሆነ  እንደ አገር ተሰፋ ሰጪ እምርታ ማስመዝገብ ይቻላል ብለዋል፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግ ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰቡ ዘንድ ያሉ አንገብጋቢ ችግሮች ላይ ያተኮሩ የፈጠራና የምርምር ፕሮጅክቶችን በተለየ መልኩ በመደጎም ረገድ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡
በዚህ ረገድም ዩኒቨርሲቲው በአካባቢው በቅርበት በሚገኙ የገጠር ጤና ጣቢያዎችንና ትምህርት ቤቶችን ከፀሐይ ብርሃን በሚገኝ ሀይል የኤሌትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማስቻል ሥራዎች መከናወናቸው በዚህ ረገድ ለአብነት የሚጠቀስ ተግባር መሆኑንና በቀጣይም በሌሎችም መስኮች አገልግሎቱ በጥራትና በሽፋን ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲያድግ በማድረግ የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የማስፋት ሥራዎች በትኩረት እንደሚሠሩ ዶ/ር ዳምጠው ገልፀዋል፡፡ ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ


የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አለማየሁ ጩፋሞ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እራሱን ችሎ ከተቋቋመ በኋላ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የዘርፉን የመጀመሪያ ስምፖዚዬም ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ ዓውድ ጥናቱ  በምህንድስና እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ካሉ ችግሮች በመነሳት እና ፈጠራዎችን በማጎልበት ዘርፉን ለዘላቂ ልማት ማዋል በሚቻልበት አግባብ ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በዘርፉ የተሰሩ ሳይንሳዊ የጥናትና የምርምር ውጤቶችን በማስተቸት በተመራማሪዎች፣ በባለሙያዎች፣ በፈፃሚዎች እንዲሁም በአስፈፃሚዎች አካላት መካከል ቅንጅታዊ አሰራር እንዲጎለብትና  የእውቀትና የልምድ ልውውጥን በማሻገር አገሪቱ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን ለማድረግ እድል የሚፈጥር መድረክ እንደሆነም  ዶ/ር ሙሉነህ ገልፀዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይን እና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ሥራ አስፈፃሚ እና የእለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ነገደ አባተ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በሁሉም አገራት ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችና ኢኮኖሚው በአብዛኛው ከቴክኖሎጂና ምህንድስና ዘርፍ በሚገኙ የምርት ውጤቶች ላይ ጥገኛ እንደሆነ ተናግረው ዘርፉ መሠረተ ልማቶችን ጨምሮ፣ የቤት፣ የሀይል፣ የውሃና ሌሎች ማሕበራዊ አገልግሎቶችን ወደ ተጠቃሚው ከማድረስ አንጻር እንዲሁም ኢኮኖሚውን ወደ ኢንደስትሪ መሪ ለማሸጋገር ጉልህ ሚና የሚጫወት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ዘርፍ እየታዩ ያሉና በከፍተኛ መጠን እያደጉና በዓይነትም ውስብስብ የሆኑ ችግሮችን የመቅረፍ ኃላፊነት በአገሪቱ ባሉ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትከሻ ላይ ያረፈ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ነገደ የሚካሄዱ የጥናትና የምርምር እንዲሁም የፈጠራ ሥራዎች በዋናነት በተናጥል ከመስራት ይልቅ በጋራ መሥራቱ  እውቀትና ልምድን ከመለዋወጥ ባሻገር ትልልቅ የሆኑ አገራዊ ፕሮጀክቶች ስኬታማ እንዲሆኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስለሚያበረክት ትልቅ ትኩረት ሊሠጠው ይገባል ብለዋል፡፡
በአገራዊ ዓውደ ጥናቱ በኤሌክትሮ-መካኒካል ምህንድስና፣ በመረጃ ቴክኖሎጂና ኮምፒዩቲንግ፣ በምቹ አካባቢ ግንባታ ዘዴዎችና ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮሩ ከ14 በላይ የምርምርና 4 የፖስተር ሥራዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
ከቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፎች መካከል የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መ/ርት መንበረ አክልሉ በመንገድ ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ባድረጉት ጥናት እንደጠቆሙት በኢትዮጵያ የተሠሩና እየተሰሩ የሚገኙ መንገዶች የባለሞተር ተሸከርካሪዎችን ብቻ  ማስተናገድ እንዲችሉ ተደርገው መሠራታቸው የመንገዱን ጠቀሜታ ከማሳነሱም ባሻገር አብዛኛው በገጠር የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል የሚጠቀሟቸውን ሞተር አልባ ተሸከርካሪዎች ያገናዘበ ባለመሆኑ በመንገድ ላይ በሚያመጡት ጫና ለትራፊክ አደጋ እና መጨናነቅ አንዱ መንስኤ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡  የመንገዶች ዲዛይን እና ግንባታ ሥራ የሞተር አልባ ተሸከርካሪዎችን ባገናዘበ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡
ሌላኛው በDr Santhosh K. በእጅ የሚንቀሳቀስ የሸንኮራ አገዳ መጭመቂያ ማሽን ንድፍ የቀረበ ሲሆን አቅራቢው በኢትዮጵያ በቆዩበት 4 ዓመታት ሸንኮራ አገዳ በየገበያው በስፋት እየተሸጠ የሚገኝ ቢሆንም አምራቾች ለራሳቸውም ሆነ ለኢንደስትሪው ግብዓት በሚሆን መልክ ሲጠቀሙ ባለመመልከታቸው በቀላሉ ምርቱን ለተለያዩ አገልግሎቶች ለማዋል የሚያስችል ማሽን ለመስራት እንደተነሳሱ ተናግራዋል፡፡ ይህንን ማሽን በመጠቀም ጭማቂ በማምረት ለምግብነትም ሆነ  ለገበያም በቀላሉ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻልም Dr Santhosh K. ተናግረዋል፡፡ 
ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት መሰል የምርምር ማህበረሰብ ጉባዔ መካሄዱ በአብዛኛው በምህንድስና እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች የሚሠሩ ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎች ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያግዝ ነው፡፡ በተጨማሪም  የተለያዩ አገራዊ ልማቶችን በቅንጅት መሥራት እንደ አገር የሚሰሩ ፕሮጀክቶች በተናጥል በመሠራታቸው ምክንያት የሚፈጠሩ ጉድለቶችን ለማረም የሚያስችል እድል እንደሚፈጥር ተሳታፊዎቹ ገልፀዋል፡፡ መንግስትም በዚህ መልኩ በጥናት ተደግፈው የሚቀርቡ  ሀሳቦችንና የፈጠራ ውጤቶች ወደ ሕብረተሰቡ ወርደው ተግባረዊ እንዲሆኑ የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባልም ብለዋል፡፡
በዓውደ ጥናቱ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎች፣ መምህራን፣ የድኅረ-ምረቃ ተማሪዎች፣ የቀድሞ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣ ከሲቪል ሰርቪስ፣ ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ከመዳ ወላቡ፣ ከመቐለ፣ ከአሶሳ እና ከሌሎችም 10 በላይ ከሚሆኑ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ተመራማሪዎችን ጨምሮ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት