አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፈረንሳይ አገር ኒስ ከተማ ከሚገኘው International Center for Pure and Applied Mathematics (CIMPA) ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ሚያዝያ 2/2011 ዓ/ም ተፈራርሟል፡፡ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ


የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ CIMPA በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ሰባት የሒሳብ ፕሮፌሰሮችን ወደ ዩኒቨርሲቲያችን በመላክ የተለያዩ የፒ/ኤች/ዲ ኮርሶችን በመስጠት ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው ፐሮፌሰሮቹ ሴሚናሮችን በማዘጋጀት ለትምህርት ክፍሉ መምህራን ልምድና አዳዲስ ዕውቀቶችን አካፍለዋል ብለዋል፡፡ ስምምነቱ በሁለቱ ተቋማት መካከል የተጀመረውን መልካም ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ እንደሆነና ዩኒቨርሲቲው በትኩረት እየሠራ የሚገኘውን የዓለም አቀፋዊነት ሥራ እንደሚያጠናክር ዶ/ር የቻለ በስምምነቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡
እንደ ዶ/ር የቻለ ገለጻ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የሚደረጉ ስምምነቶች ለዩኒቨርሲቲው ተልዕኮና ራዕይ ስኬት ጉልህ ሚና የሚጫወቱ በመሆናቸው ለስምምነቶቹ ተግባራዊነት ዩኒቨርሲቲው በትኩረት ይሠራል፡፡ ከCIMPA ጋር ግንኙነት በመፍጠር ዩኒቨርሲቲው ተጠቃሚ እንዲሆን ላስቻሉትና ግንኙነቱ እንዲጠናከርና ተቋማቱ የመግባቢያ ስምምነት እንዲፈራረሙ ጉልህ አስተዋጽኦ ላበረከቱት ለካሜሩናዊው የዩኒቨርሲቲው መምህር ዶ/ር Patrick Tchepuao እና የሒሳብ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ለሆኑት ዶ/ር ስምዖን ደርኬ በዩኒቨርሲቲው ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የCIMPA ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር Ludovic Rifford በበኩላቸው ማዕከሉ የሒሳብ ትምህርትንና በመስኩ የሚሠሩ የምርምር ሥራዎችን በታዳጊ አገሮች ለማስፋፋት እንደተቋቋመ አስታውሰው ተቋሙ ከፈረንሳይ ባሻገር በስዊድን፣ ኖርዌይና ሲውዘርላንድ እንደሚደገፍ ተናግረዋል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ ገላፃ ማዕከሉ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር የጀመረውን ግንኙነት በማጠናከር በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ቅርንጫፍ የሒሳብ ትምህርት ቤት የሚከፍት ሲሆን በዚህም ለሌሎች የኢትዮጵያም ሆነ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የስኮላርሺፕ ዕድል እንደሚሰጥና የፒ ኤች ዲ ፕሮግራሞችም እንደሚኖሩ  ተናግረዋል፡፡
በስምምነቱ የዩኒቨርሲቲውን ጥያቄና ፍላጎት መሠረት በማድረግ CIMPA የተለያዩ የPHD እና የማስተርስ አድቫንስድ ኮርሶችን የሚሰጡ ፕሮፌሰሮች የሚልክ ሲሆን ወጪያቸውም ከመኝታና ከምግብ በስተቀር በማዕከሉ የሚሸፈን ይሆናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በስምምነቱ እንደተጠቀሰው የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችና መምህራን በተለየዩ የዓለም ክፍሎች በሚገኙ የCIMPA የምርምርና የሒሳብ ትምህርት ቤቶች እንዲሳተፉ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፤ ይህም ተማሪዎቹ የምርምር አማካሪዎችን እንዲያገኙ ትልቅ ዕድል መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት