የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ከምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በእንቦጭ አረምና በአኩሪ አተር ጠቀሜታ ዙሪያ ከኢንዶኔዥያ በመጡ የመስኩ ባለሙያዎች ለኮሌጁ መምህራንና ተመራማሪዎች መስከረም 12/2015 ዓ/ም የአሠልጣኞች ሥልጠና ሰጥቷል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕሮፌሰር በኃይሉ መርደኪዮስ እንደገለጹት እንቦጭ አረም በአቅራቢያችን በሚገኘው ዓባያ ሐይቅና በሌሎችም የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች በከፍተኛ ሁኔታ በመዛመት ላይ ይገኛል፡፡ የአካባቢውን ወጣቶች በማኅበራት አደራጅቶ አረሙን በመጠቀም የተለያዩ ሥራዎችን እንዲሠሩ ማድረግ የአረሙን መስፋፋት በመቀነስ የተጋረጠውን አደጋ ለመቅረፍ ብሎም የሥራ እድል ለመፍጠር የሚረዳ መሆኑን ም/ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

ኢንዶኔዥያ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ችግር ውስጥ የነበረችና በአሁኑ ወቅት ችግሩን ወደ መልካም አጋጣሚ ቀይራ መጠቀም የቻለች በመሆኑ ተሞክሮዋን መካፈሉ ወሳኝ መሆኑን ም/ፕሬዝደንቱ ገልጸው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም እንቦጭ አረም ጥቅም ላይ እንዲውል በምርምር ለመደገፍና ሥልጠናውን ለአካባቢው ወጣቶች በማዳረስ ወደ ተግባር እንዲቀይሩ ጠንክሮ ይሠራል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ፣ ጅቡቲና አፍሪካ ኅብረት የኢንዶኔዥያ አምባሳደር አል ቡስራ ባስኑር/Al Busyra Basnur/ በአኩሪ አተርና በእንቦጭ አረም ላይ የሚደረገው የልምድ ልውውጥ ከዚህ ቀደም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከኢንዶኔዥያ 17 ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ያደረገው ስምምነት አካል ሲሆን በቀጣይም በዘርፉም ሆነ በሌሎች መሰል ተግባራት ምርጥ ተሞክሮዎችን በመጋራት  የተሻሉ ሥራዎችን እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ብርሃኑ ለማ ለሀገራችን ስጋት የሆነውን እንቦጭ አረም ከጉዳቱ ባሻገር ያሉትን ጠቀሜታዎች የኢንዶኔዥያን ተሞክሮዎች በመውሰድና እንደ ሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ቀምሮ ተግባር ላይ በማዋል ምርትና ምርታማነትን መጨመር የሥልጠናው ዓላማ ነው ብለዋል፡፡ ዶ/ር ብርሃኑ አክለውም ከአኩሪ አተር የሚሠሩ ምግቦችን በቀላሉ ማዘጋጀት እንደሚቻል በቂ ግንዛቤን በመጨበጥ ልምዱን ወደ ግለሰብና ተቋም እንዲሁም ወደ ማኅበረሰብ ተደራሽ በማድረግ ጥቅም ላይ እንዲውል እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

በኢንዶኔዥያው ስሪዊጃ ዩኒቨርሲቲ /Sriwija University/ መምህር የሆኑት ፕ/ር ሙላዋራማን /Mulawaraman/ በሰጡት ሥልጠና የእንቦጭ አረም ለዶሮ፣ ለፍየልና በግ መኖነት እንዲሁም ለባዮጋዝ መሥሪያነት እንደሚያገለግል የገለጹ ሲሆን ግንዱን በመጠቀም የተለያዩ ጌጣጌጦችና የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች መሥራት እና የእንቦጭ አረምን ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያነት /Organic Compost/ የመቀየር ሂደት በተግባር አሠልጥነዋል፡፡

ሌላኛው አሠልጣኝ የኢንዶኔዥያው አምባሳደር የግል ሼፍ አዲ ፑትራ ካንድራ /Adi Putra Candra/ በሰጡት ሥልጠና አኩሪ አተርን በመጠቀም የሚዘጋጁ የአኩሪ አተር ወተት /Soybean Milk/፣ የአኩሪ አተር ዘይት /Soybean Oil፣ ባህላዊ የኢንዶኔዥያ ምግብ /Soybean Tempe/ እና ሌሎችም የተለያዩ ምግቦችን በተግባር በማዘጋጀት አሳይተዋል፡፡ አኩሪ አተር ስብ፣ ኃይል ሰጪ፣ ብረት፣ ቫይታሚን፣ ፖታሲየም፣ ማግኒዚየም እና ሶዲየም የመሳሰሉ ንጥረ ነገሮችን የያዘ በመሆኑ አዘውትሮ መጠቀሙ ለሰውነታችን ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚሰጥ አሠልጣኙ ጠቁመዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው በእንቦጭ አረምና አኩሪ አተር ጠቀሜታ ላይ ያላቸውን ግንዛቤ በተጨባጭ እንዳሰፋላቸውና በቀጣይ በዘርፉ የተለያዩ ምርምሮችን በማካሄድ ያገኙትን ተሞክሮ ወደ ተግባር በመቀየር እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት