የዩኒቨርሲቲው የተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል ከጤና ሚኒስቴር ጋር በተደረገ ስምምነት መሠረት በሚኒስቴሩ አማካኝነት የተደረገን የመድኃኒት ስርጭት ሽፋን ማረጋገጫ ዳሰሳ ጥናት ለማከናወን በአራት ክልሎችና በአንድ ከተማ አስተዳደር ሥራውን ለሚያከናውኑ መረጃ ሰብሳቢዎች ከመስከረም 18-19/2015 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ በጤና ሚኒስቴር የተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎችን ለመከላከል የሚደረገውን የመድኃኒት ስርጭት በኮሌጁ የሚገኘው የምርምርና ሥልጠና ማዕከል ገለልተኛ አካል በመሆን የሽፋን ማረጋገጫ ዳሰሳ ጥናትን በተደጋጋሚ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ ጥናቱ በአስቸጋሪ ሁኔታና ቦታዎች ላይ በመገኘት የሚሠራ ሲሆን ሠልጣኞች በሥልጠናው የሚያገኙትን ግንዛቤ በመጠቀም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የተሰጠንን ሀገራዊ ኃላፊነት በአግባቡ ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

የማዕከሉ ዳይሬክተር ረ/ፕ ጸጋዬ ዮሐንስ በበኩላቸው የምርምርና ሥልጠና ማዕከሉ በ2014 በጀት ዓመት ብቻ ከደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር በሌሽማኒያ በሽታ ሕክምና አሰጣጥ ዙሪያ እንዲሁም እዩ-ኢትዮጵያ ከተሰኘ ድርጅት ጋር በመተባበር የተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ቁጥጥርና ሕክምና አሰጣጥን ከዘመቻ ሥራ በማውጣት ወደ መደበኛው የጤና ሥርዓት ውስጥ እንዲካተት በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ዕቅዱ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን ለማወቅ የሚረዳ ጥናት በማከናወን ሪፖርቱን አጠናቆ ማቅረቡን ጠቅሰዋል፡፡

በሽታዎቹን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንጻር እንደ ሀገር ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል  ቢልሃርዚያ፣ የአንጀት ጥገኛ ትላትልና እንደ እከክ ያሉ በሽታዎችን ለመከላከል የሚደረገው ሰፊ የመድኃኒት ሥርጭት አንዱ ሲሆን ማዕከሉ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በተፈራረመው የመግባቢያ ስምምነት መሠረት የመድኃኒት ስርጭት ሽፋን ማረጋገጫ ዳሰሳ እንዲያከናውን በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት በመረጃ መሰብሰብ ሥራ ላይ ለሚሠማሩ መምህራን ሥልጠናው መዘጋጀቱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ሥልጠናው በዋናነት በመረጃ አሰባሰብ ዘዴዎች፣ መጠይቆችና ቦታዎችና ለሥራው በተዘጋጀ የሞባይል መተግበሪያ አጠቃቀም ላይ ያተኮረ ሲሆን ሥልጠናው ጥራት ያለው መረጃ ከመሰብሰብ አንፃር የጎላ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

በዘርፉ አጋር በመሆን ከጤና ሚኒስቴር ጋር በትብብር ከሚሠራው ‹‹Schistosomiasis Control Initiative›› የመጡት አቶ ብርሃኑ ጌታቸው የተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎችን ከመቆጣጠር አንጻር ተጋላጭ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚደረገው የመድኃኒት ዕድላ ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰው የዚህም ሥራ ክንውን ሪፖርት በየጊዜው በወረዳዎች አማካኝነት ይቀርባል ብለዋል፡፡ እንደ አሠራር የቀረቡ ሪፖርቶችን በገለልተኛ አካል ማረጋገጥ ስለሚገባ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል በዘርፉ ካለው ልምድ አንጻር የስርጭት ሽፋን ማረጋገጫ ዳሰሳውን እንዲያከናውን ተመርጧል ብለዋል፡፡ ማዕከሉ በዘርፉ እንደ ሀገር ከሚሠሩ ተቋማት መካከል ግንባር ቀደም መሆኑን የገለጹት አቶ ብርሃኑ ለዚሁ ሥራ የሚውለው ወጪ እንዲሁም ለሥራው የሚያግዘውን መተግበሪያ የያዙ 40 ተንቀሳቃሽ ስልኮች በፋውንዴሽኑ የተሸፈኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከሠልጣኞች መካከል በኮሌጁ የኅብረተሰብ ጤና ት/ቤት መምህርት ሕይወት ታደሰ በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው ከመሠረታዊ ጉዳዮች ጀምሮ የመድኃኒት ስርጭት ሽፋን ማረጋገጫ ዳሰሳ ለማከናወን ትክክለኛ መረጃ የሚሰበሰብባቸው ዘዴዎችና ሥራው በሚከናወንባቸው ቦታዎች ላይ በመመሥረት የተሟላ ግንዛቤ የፈጠረ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር መረጃው የሚሰበሰበው ቴክኖሎጂን በመጠቀም በመሆኑ ለዚሁ ሥራ የተዘጋጀውን የሞባይል መተግበሪያ አጠቃቀም በስፋት ያዩበትና ጥራት ያለው መረጃ መሰብሰብ የሚያስችል ግንዛቤ የተፈጠረበት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

የመድኃኒት ስርጭት ሽፋን ማረጋገጫ ዳሰሳው በኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ ሐረሪ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሚከናወን ይሆናል፡፡
                                                                                                                                                                                                        የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት