አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከጋሞና ጎፋ ዞኖች እንዲሁም ከጀርመኑ ሰሃይ ሶላር ማኅበር ጋር ለቀጣይ ሦስት ዓመታት በታዳሽ ኃይል ዙሪያ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት የካቲት 1/2015 ዓ/ም ተፈራርሟል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የትብብር ሥራው ለማኅበረሰቡ የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰው የጤና ተቋማትንና ት/ቤቶችን አገልግሎት በማሻሻል ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡ የትብብር ፕሮጀክቱ ከዩኒቨርሲቲው ተልእኮና ቴክኖሎጂ ሽግግር ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ያለው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የስምምነት ፕሮጀክቱ በርቀት ላይ በሚገኙ ገጠራማ አካባቢዎች በምርምር የተደገፉ ተጨማሪ ሥራዎችን ለመሥራት ዕድል የሚፈጥር እንደሆነም ዶ/ር ዳምጠው ጠቅሰዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕሮፌሰር በኃይሉ መርደኪዮስ ፕሮጀክቱ በእስከአሁን ቆይታው የተለያዩ ውጤታማ ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው የፕሮጀክቱን ጉዞና አፈጻጸም ለማወቅ በተካሄደ ግምገማ የሕፃናትና እናቶችን ሕይወት ከመታደግ፣ የሥራ ዕድል ከመፍጠር፣ ማኅበራዊ ትስስርን ከማጠናከር፣ ለኑሮ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር፣ የትምህርት ዕውቀትን ከማስፋፋትና ገቢን ከማሳደግ አንጻር የላቀ አፈጻጸም የተመዘገበበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ ም/ፕሬዝደንቱ በተፈረመው ስምምነት መሠረት የተለያዩ ጤና ጣቢያዎችና ት/ቤቶችን የሶላር ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ፣ በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ የመስኖና የንጹሕ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን ማከናወን፣ ተጨማሪ የምርምር ሥራዎችን መሥራትና በመስኩ ያለውን የአጠቃቀምና የጥገና ክሂሎት የሚያሻሽሉ ሥልጠናዎችን መስጠት ላይ በማተኮር እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡  

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በዞኑ በፕሮጀክቱ አማካኝነት ሲሠሩ የቆዩ ሥራዎች አበረታችና አስደሳች መሆናቸውን ገልጸው በፕሮጀክቱ የተከናወኑ ተግባራት ማኅበረሰቡንና ተቋማትን የጠቀሙ ናቸው ብለዋል፡፡ በአሁኑ የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ለሚሠሩ ጠቃሚ ሥራዎች የዞኑ አስተዳደር የሚጠበቅበትን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል፡፡

የጎፋ ዞን ም/አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም ዞራ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በርቀት አካባቢ የሚገኙ የጤና ተቋማትንና ትምህርት ቤቶችን የመብራት ኃይል ለማዳረስ መንግሥት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የሚደግፍ ነው ብለዋል፡፡ ቀጣይ በሚሠሩ ሥራዎች መካከል በገጠር ላሉ ወጣቶች ከጥገና ጋር የተያያዙና ሌሎች ሥልጠናዎች የሚሰጡ በመሆኑ በፕሮጀክቱ ጊዜ የሚሠሩ ሥራዎች ለረዥም ጊዜ እንዲቆዩ ያስችላል ብለዋል፡፡

የሰሃይ ሶላር ማኅበር መሥራችና የጀርመን ቅርንጫፍ ተወካይ ማክስ ፖል ፕሮጀክቱ በዋናነት የማኅበረሰብ ጉድኝት፣ ቴክኖሎጂ ሽግግርና አቅም ግንባታን ዓላማ አድርጎ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ ባለፉት ዓመታትም በፕሮጀክቱ ዘጠኝ የ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶችና 23 የገጠር ጤና ጣቢያዎች የፀሐይ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ሶዴሳ ሶማ የትብብር ፕሮጀከቱ ከ2009 ዓ/ም ጀምሮ ሲሠራ መቆየቱንና ት/ቤቶችንና ጤና ጣቢያዎችን የኤሌትሪክ ተጠቃሚ ከማድረጉ ባሻገር ለ300 የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችና ለ200 የዘርፉ መምህራንና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች መስጠቱን ገልጸዋል፡፡ በስምምነቱ መሠረት የምርምር ማዕከሉ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የሚጠበቅበትን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም አቶ ሶዴሳ ተናግረዋል፡፡

                                                                                                                                                የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
                                                                                                                                             የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት