Print

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት ከጥር 2011 ዓ/ም ጀምሮ በአርባ ምንጭ፣ ሳውላና በዩኒቨርሲቲው ኮሚዩኒቲ 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ሲካሄድ የነበረው በICT መሣሪያዎች የተደገፈ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማስተማሪያ ስነ ዘዴ ማሻሻያ ግራንድ የምርምር ፕሮጀክት የመዝጊያ መርሃ ግብር ጥር 4/2015 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ቋንቋ የአንድ ማኅበረሰብ መግባቢያና የማንነቱ መገለጫ መሆኑን ጠቅሰው እንግሊዝኛ ቋንቋ በዓለም ላይ ከፍተኛ የተናጋሪ ቁጥር ያለውና የሳይንስ፣ የቱሪዝም፣ የቴክኖሎጂ፣ የመገናኛ ብዙኃንና የበይነመረብ ቋንቋ ነው ብለዋል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ እንግሊዝኛ ቋንቋን ከመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ጀምሮ እንደ ዓለም አቀፍ ቋንቋ ትምህርት እየሰጠችበት ነው ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ በዩኒቨርሲቲው የICT መሣሪያዎችን በመጠቀም የመምህራንና የተማሪዎችን የቋንቋ ችሎታና የማስተማሪያ ስነ ዘዴ ለማሻሻል በግራንድ የምርምር ፕሮጀክት ደረጃ ሲሠራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ የመምህራንን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታና የማስተማሪያ ስነ ዘዴ ማሻሻል የትምህርት ተቋምን፣ ግለሰብን፣ ማኅበረሰብንና ሀገርን ማሳደግ መሆኑን ተገንዝበው በየደረጃው ያሉ ተሳታፊዎች በየጊዜው ራሳቸውን መፈተሽና ከዘመኑ ጋር የሚጓዝ የሠለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ተግተው መሥራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የገንዘብ ድጋፍ ‹‹የICT መሣሪያዎችን በመጠቀም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማስተማሪያ ስነ ዘዴን ማሻሻል/Improving English Language Teaching Through ICT Tools›› በሚል ርዕስ ጥር 2011 ዓ/ም መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ተስፋዬ ፕሮጀክቱ በትምህርት ክፍል ብቻ ተወስኖ የነበረውን የእንግሊዝኛ ቋንቋ አጠቃቀም መምህራንና ተማሪዎች ከክፍል ውጭ እንዲጠቀሙና የመምህራንን የማስተማሪያ ስነ ዘዴ ለማሻሻል ያለመ ሲሆን በውጤቱም በአራቱም የቋንቋ ክሂሎቶች ማስተማሪያ ስነ ዘዴ በመምህራን ላይ ከፍተኛ መሻሻል እንዲሁም በአሠልጣኝነት የተሳተፉ የICT መምህራንና የላቦራቶሪ ቴክኒሻኖች የክሂሎት እድገት ታይቷል፡፡

በጥናቱ የተሳተፉ ሦስት የ2ኛና የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች የመመረቂያ ጽሑፎች በታዋቂ ዓለም ዓቀፍ ጆርናሎች ላይ መታተማቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት በሚሰጥባቸው የትምህርት ዓይነቶች ለሚያስተምሩ መምህራን ሥልጠናውን ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ኮሚዩኒቲ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር የሆኑት የፕሮጀክቱ ሠልጣኝ መ/ር ታሪኩ ዴአ በአስተያየታቸው በፕሮጀክቱ በመሳተፌ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የማስተማር ክሂሎት ላይ መሻሻል አሳይቻለሁ ብለዋል፡፡
በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ለሠልጣኞች የምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት