Print

 የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት በጨንቻ ዙሪያ ወረዳ በሚገኘው ሻማ ጎማ፣ ቀርጴ እና በሌ ቀርጴ መንደሮች ላይ በ1.9 ሚሊየን ብር ያስገነባውን የሻማ ቀበሌ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የካቲት 12/2015 ዓ/ም አስመርቋል፡፡ ከፕሮጀክት ሥራው 400 ሺህ ብር ወጪ የተሸፈነው ማኅበረሰቡ በጉልበቱ ባበረከተው አስተዋፅዖ ነው፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተልዕኮዎች መካከል የማኅበረሰብ አገልግሎቶችን መስጠት አንዱ እንደመሆኑ ዩኒቨርሲቲውም ለአካባቢው ማኅበረሰብ በጉድኝት የሚሠሩ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ሲሆን ለአብነትም የሻማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጠቃሽ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የአካባቢው እናቶችና ሕፃናት በውሃ ፍለጋ የሚያጠፉትን ጊዜና ጉልበት በመቆጠብ ሕፃናት በትምህርት ላይ የሚሆኑበትን ዕድል የሚጨምር በመሆኑ በአካባቢው ያሉ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶች እንዲሁም የማኅበረሰቡ አኗኗር እንዲዘምን ማኅበረሰቡ ለትምህርት ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት ልጆቹን በጥንቃቄ እንዲማሩ ማገዝ ይገበዋል ያሉት ዶ/ር ዳምጠው ዩኒቨርሲቲው የሚያከናውናቸው መሰል የልማት ተግባራት ሀገራችን በየዘርፉ እያስመዘገበች የምትገኘው የዕድገትና የልማት ሥራዎች አካል መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

የጋሞ ዞን የካቢኔ ጉዳዮች አማካሪ እና የዞኑ አስተዳደር ተወካይ አቶ እሸቱ ኤልቶ መንግሥት ለእያንዳንዱ ኅብረተሰብ በየአቅራቢያው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየሠራ ቢሆንም እንደዞኑ ተጨባጭ ሁኔታ የንጹህ መጠጥ ውሃ የሚያገኘው የኅብረተሰብ ክፍል አነስተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው የኅብረተሰቡን የውሃ ችግር ለመፍታት ፕሮጀክቱን ቀርጾ ዕቅዱን እውን ማድረጉ አስዳሳች ሲሆን በቀጣይም በዩኒቨርሲቲው የሚማሩ ተማሪዎች በቆይታቸው ያገኟቸውን ዕውቀትና መልካም ተሞክሮዎች ወደማኅበረሰቡ በተግባር በማውረድ በየአካባቢያቸው የሚስተዋለውን የማኅበረሰብ ችግር በመፍታት አኗኗር እንዲሻሻል ሊሠሩ እንደሚገባ አቶ እሸቱ አሳስበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተባባሪ ፕሮፌሰር በኃይሉ መርደኪዮስ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የውሃ ፕሮጀክቶች ያሉበት ቦታ በመሄድ እንዲሁም የፀሐይ ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ወደብርሃን ኃይል ለመለወጥ የሚችሉ ባለሙያዎችን የማፍራት ተልዕኮ ያለው በመሆኑ ወደማኅበረሰቡ የሚሸጋገሩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ችግሮችን ከመፍታት አኳያ ሰፊ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ የውሃው ፕሮጀክቱ ከሕዝቡ በመጣ ጥያቄ መነሻነት ወደተግባር የተለወጠ የማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራ ሲሆን በዚህም ከንጹህ መጠጥ ውሃ ዕጥረት የሚመጡ ዘርፈ ብዙ የጤና ዕክሎችንና የተለያዩ እንግልቶችን መቀነስ የሚያስችል ሥራ መሠራቱንም ጠቁመዋል፡፡ ተባባሪ ፕሮፌሰር በኃይሉ የውሃው ምንጭ ሳይደርቅ ወደፊት እንዲቀጥል የተገነቡት ውሃ ማጠራቀሚያዎችና ቦኖዎች ከሰውና ከከብቶች ንክኪ ነጻ እንዲሆኑ በማድረግና ውሃን የሚያደርቁ ተክሎችን ከአካባቢው በማራቅ ምንጩ የጎለበተበትን አካባቢ ሀገር በቀል ዛፎችን በመትከል፣ በመጠበቅና በመንከባከብ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሠጥ ማድረግ ተገቢ መሆኑን አሳስበዋል፡፡

በፕሮጀክቱ የማኅበረሰብ ተኮር ሥራዎች እጅግ ውስብስብ መሆናቸውን ያየንበት ነው ያሉት የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ፕሮጀክቱ ሐምሌ 2014 ዓ/ም የተጀመረ ሲሆን በቆይታውም የምንጩ የውሃ ፍሰት መጠን በበጋና ክረምት ወቅቶች አስተማማኝ መሆኑን የማረጋገጥ፣  የ2 ሜትር በ1.5 ሜትር ስፋት ያለው  የውሃ መሰብሰቢያ ጉድጓድ በመገንባት ምንጩን የማጎልበትና ሃያ አምስት ሺህ ሊትር ውሃ የሚያጠራቅም ሳንድዊች የውሃ ገንዳ በመገንባት ለሦስቱም መንደር ነዋሪዎች በስድስት ቦኖዎች እንዲያሠራጭ የሚያስችል ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህም በመንደሩ ያሉ 4,600 የሚሆኑ ነዋሪዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው ከፍተኛ የውሃ ችግር ከመኖሩ የተነሳ በጣም ርቀው በመሄድ  ንጽህናው በአግባቡ ያልተጠበቀ ውሃ እየቀዱ እንደሚጠቀሙና የራሳቸውንና የቤተሰቦቻቸውን የግል ንጽህና ለመጠበቅ በመቸገራቸው ምክንያት ለተለያዩ በሽታዎች ተጋላጭ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ዩኒቨርሲቲው በየአቅራቢያቸው ንጹህ የመጠጥ ውሃ በቀላሉ እንዲያገኙ ያደረገ በመሆኑ ችግራቸው እንደሚቀረፍላቸው ገልጸው የላቀ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ አክለውም በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው በተመሳሳይ ሁኔታ ሌሎች ችግሮቻቸውን በጥናትና ምርምር ለመፍታት ከጎናቸው ይሆን ዘንድ ጠይቀዋል፡፡

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የጋሞ ዞንና የጨንቻ ዙሪያ ወረዳ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ መምህራን፣ ተመራማሪዎችና ሠራተኞች፣ የሻማ ቀበሌ አስተዳዳሪና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡  በአካባባው ሽማግሌዎች  የምረቃ ሥነ-ሥርዓትም የተካሄደ ሲሆን በሥራው ሂደት የጎላ አስተዋጽዖ ላበረከቱ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራንና ሠራተኞች የቀበሌው አመራሮችና የአካባቢው ማኅበረሰብ የተለያዩ የምስጋና ስጦታዎችንና የምስክር ወረቀት አበርክተዋል፡፡

 

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት