Print

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት በደንበኛ አያያዝ፣ ፈጣን አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም አመራርነት ክሂሎት ዙሪያ ከ5ቱም ካምፓሶች ለተወጣጡ ሴት መምህራን፣ የአስተዳደር ሠራተኞችና አመራሮች ከየካቲት 9-10/2015 ዓ/ም ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገዝሙ ቃልቦ እንደገለጹት ባለንበት ዘመን ሴቶች ከዚህ ቀደም ካለው በተሻለ መልኩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ተሳትፈው ብቃታቸውን እያሳዩ ይገኛል፡፡ ከፍተኛ የአመራር ቦታ ላይ የደረሱትን በመመልከት ሁሉም ሴቶች ወደአመራርነት ለመምጣት የሚችሉ መሆኑን መገንዘብ እንደሚኖርባቸውም የጽ/ቤቱ ኃላፊ ተናግረዋል፡፡

የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወሪ/ት ሠናይት ሳህሌ ለሴት የአስተዳደር ሠራተኞች በደንበኛ አያያዝና ቀልጣፋ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የተሰጠው ሥልጠና ወደዩኒቨርሲቲው የሚመጡ ተገልጋዮችን በአግባቡ እንዲያስተናግዱ ለማስቻል እንዲሁም የደንበኞችን እርካታ ከፍ ለማድረግ ታልሞ የተዘጋጀ ነው፡፡ በአመራርነትና ክሂሎት ዙሪያ የተሰጠው ሥልጠናም ሴቶችን ወደአመራርነት ለማምጣት ያለመ ሲሆን ከወንዶች እኩል የአመራርነት የማስፈፀም አቅምን በማጎልበት የራሳቸውን ሚና ለመወጣት በትጋት መሥራት ከሴቶች የሚጠበቅ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቡድን መሪ አቶ ዛፉ ዘውዴ ጾታ በተፈጥሮ የሚመጣ መለወጥ የማይቻል ወንድ ወይም ሴት የመሆን ጉዳይ መሆኑን ገልጸው በተለይ ሴቶች ላይ የሚደርሰው ጾታዊ ጥቃትና ትንኮሳ ከግንዛቤ እጥረት የሚመነጭ መሆኑን ተናገረዋል፡፡ ለወንድና ለሴት ተብሎ የሚደረግ የሥራ ድርሻ ክፍፍል ሊኖር አይገባም ያሉት አቶ ዛፉ ችግሮችን ለመቅረፍ መሰል ሥልጠናዎችን ማዘጋጀት ተገቢ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሰው ሀብት አስተዳደርና ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ከአምላክነሽ ደሳለኝ ‹‹የደንበኛ አያያዝና ፈጣን አገልግሎት አሰጣጥ›› በሚል ርዕስ በሰጡት ሥልጠና የባለጉዳይ ማንነት፣ ፍላጎት፣ የተገልጋይ ባህርይ፣ የመንግሥት አገልግሎት ምንነት፣ ጥራት ያለው አገልግሎት መጓደል መፍትሄዎችና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ  ሰፊ ገለጻ አድርገዋል፡፡

በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በሕክምና ላቦራቶሪ ሳይንስ ት/ክፍል መምህርትና የኮሌጁ የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሪት ገሊላ ቢረሳው የመሪነት ምንነት፣ የመሪነት መገለጫዎች፣ ሴቶች በመሪነት ላይ ያላቸው ችሎታና አቅም ዙሪያ ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡ መ/ርት ገሊላ ሴቶች በተፈጥሮ ትዕግስተኛ፣ አድማጮችና አድናቂዎች በመሆናቸው ከወንዶች በተሻለ የመምራት ችሎታ እንዳላቸው ጠቅሰው ስለሆነም ሴቶች ውስጣቸው ያለውን ፍርሃትና የአልችልም ስሜትን ማስወገድ ይኖረባቸዋል ብለዋል፡፡ 

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው መነቃቃትን የፈጠረና በርካታ ግንዛቤዎችን ያገኙበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት