የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዳይሬክቶሬት 9ኛውን ሀገር አቀፍ ምርምር ለልማት ዓውደ ጥናት ከየካቲት 17-18/2015 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በ‹‹Norwegian University of Life Sciences›› የኢኮኖሚክስና ቢዝነስ ት/ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር መስፍን ጥላሁን ባቀረቡት ቁልፍ ንግግር ሳይንሳዊ የሆኑ ምርምሮች የሀገሪቷንና የኅብረተሰቡን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ተፈጥሮሀብታዊ ችግሮች ከስሩ የሚፈቱ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ተመጋጋቢ በሆነ መንገድ ልማትና እድገትን መሠረት አድርገው ለፖሊሲና ለልማት ዕቅድ ግብዓት የሚሆኑ የየዘርፉን ዲሲፕሊን ባማከለ መንገድ ሁሉም የራሱን አስተዋጽዖ የሚያበረክትባቸው ሊሆኑ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ አክለውም የተፈጥሮ ሀብቶች በዓለምም ሆነ በሀገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሱ ያሉ በመሆኑና ከሕዝብ ብዛት አንጻር የተመጣጠነ ሀብት ባለመኖሩ በዘርፉ በጥናትና ምርምር የተደገፉ ብዙ ሥራዎችን ልማት ላይ ማዋል አለብን ብለዋል፡፡ በዚህ ረገድ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኅብረተሰቡንና ተፈጥሮን ያማከሉና ችግሮችን ሊፈቱ የሚችሉ ምርምሮችን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ዶ/ር መስፍን አሳስበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ዩኒቨርሲቲው በተከታታይነት በሀገር አቀፍ ደረጃ የጥናትና ምርምር ዓውደ ጥናት በማካሄድ ላይ ያለ ሲሆን ይህም ልምድ እስከአሁን ሳይቋረጥ የመጣና ወደፊትም የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት በጎ ተሞክሮ ነው ብለዋል፡፡ ምርምር የዩኒቨርሲቲው ተቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫ እንደመሆኑ የዘወትር ሥራና የዕለት ከዕለት ቋንቋ ሊሆን ይገባዋል ያሉት ተ/ፕ በኃይሉ ዩኒቨርሲቲው በፍጥነት የሚተገበር ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ነድፎ በተግባር ለመተርጎም በእንቅስቃሴ ላይ በመሆኑ በመተጋገዝና በብርታት በመሥራት በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ዩኒቨርሲቲውን በጥናትና ምርምር እንዲሁም በሳይንስና ፈጠራ ሥራዎች ከከፍታ ማማ ላይ ለማድረስ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም በበኩላቸው የዓውደ ጥናቱ ዓላማ በማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ በተለያዩ ቦታዎች የሚሠሩ ምርምሮችን አንድ ቦታ በማሰባሰብ ለማኅበረሰቡና ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆን ሃሳብ ማውጣት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም የኅብረተሰቡን ችግር በጥናት በመለየት ለማኅበረሰቡ የሚጠቅሙ ሃሳቦችን በማመንጨትና ወደመሬት በማውረድ ረገድ በትኩረት እንደሚሠራ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

‹‹የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የትምህርት አመራር ሚና›› በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ትምህርትና ስነ-ባህርይ ሳይንስ ት/ቤት መምህር ረ/ፕ ሰለሞን ሳጶ የትምህርት ጥራት አመላካች የሆኑ የትምህርት ግብዓት፣ ሂደትና ውጤትን በመፈጸምና በማስፈጸም ረገድ የትምህርት አመራሩን ሚና የለየ ጥናት አቅርበዋል፡፡ የትምህርት ጥራት አመላካች ከሆኑት መካከል አንዱ የባለድርሻ አካላት ሚና ሲሆን የትምህርት ግብዓት አቅርቦትን ማረጋገጥ፣ የወላጆች የልጆቻቸውን ትምህርት መከታተል እንዲሁም የትምህርት አመራር አካላትን በተለያዩ ውሳኔ ጉዳዮች መርዳት፣ የተለያዩ የትምህርት ፖሊሲዎችን በጋራ ሆኖ እንደአንድ የትምህርት ቤት አመራር ከመፈጸም አንጻር ሚናቸው መካከለኛ መሆኑ በጥናቱ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የመጡት ሌላኛው አቅራቢ ዶ/ር ዮናስ ይልማ ‹‹የደራሼ ማኅበረሰብ የባህላዊ ሕክምና ዕውቀትና ትግበራ›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ ባህላዊ ሕክምናን በመጠቀም ሀገር በቀል ዕጽዋት እንዴት እንደሚጠበቁና የኅብረተሰቡ ሚና ምን መሆን እንዳለበት ተዳሷል፡፡  በተጨማሪም የደራሼ ማኅበረሰብ በጤና፣ በሕመም እና በፈውስ ዘዴ ላይ ያለው ባህላዊ አረዳድ ምን ይመስላል የሚለውን የቃኙ ሲሆን ታሪካዊ አረዳዱ ማኅበረሰቡ ይዞት የመጣው ታሪክ፣ ባህልና ወግ እንዲሁም ማኅበረሰቡ ከተፈጥሮ ጋር ያለው ግንኙነት በእጅጉ የተቆራኘ ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ ከተለያዩ 21 ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት የተወጣጡ በማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ፣ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ ሕግ እና በስነ-ትምህርትና ስነ-ባህርይ ሳይንስ ዘርፎች ላይ ትኩረት ያደረጉ 45 ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡

                                                                                                                         አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
                                                                                                                          የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
                                                                                                                        የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት