አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ‹‹የ21ው ክፍለ ዘመን በአፍሪካ የኢትዮጵያ ስትራቴጂ/Ethiopia’s Africa Strategy for Twenty-first Century›› በሚል ርዕስ የፖሊሲ የምክክር መድረክ የካቲት 17/2015 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በዕለቱ ከቀረቡ የጥናት ጽሑፎች መካከል ‹‹Ethiopia’s Role in African Liberation and Multilateral Institution Building: A Historical Appraisal››፣ ‹‹Commentary on Ethiopia’s African policy››፣ ‹‹The Changing Global Order and Its Impact on Ethiopia’s Africa Foreign Policy›› እና ‹‹Charting Ethiopia’s African Strategic Roadmap›› ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ደሳለኝ አምባው ኢንስቲትዩታቸው የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ምክረ ሃሳቦች የሚሰጡበትና የሥልጠና ተቋም መሆኑን ገልጸው በሥልጠና ዘርፉ በዲፕሎማሲያዊ ሥልጠና፣ በባለድርሻ አካላት ሥልጠና እና ዕውቀት አስተዳደር ዘርፍ የተዋቀረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ ዋና ዳይሬክተሩ የምክክር መድረኩ የአፍሪካ ጉዳዮች የጥናትና ምርምር ዘርፍ ዳይሬክተር ጄኔራል አዘጋጅነት የቀረበ ሲሆን ዋና ዓላማውም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሊኖራትና ልትከተለው ስለምትችለው ስትራቴጂ ላይ ጥልቅ ውይይት በማድረግ የኢትዮጵያን የአፍሪካ ስትራቴጂ ፍኖተ ካርታ ማመላከት መቻል ነው፡፡ በመድረኩም አራት ዐቢይ ጉዳዮች ላይ ጥናት መቅረቡን ገልጸው የሚቀርቡ ሃሳቦችን በማጠናቀር ለመንግሥትና ለባለድርሻ አካላት በፖሊሲ ገለጻና በጥናት ውጤት ሪፖርት ተደራሽ ለማድረግ ጥሩ ግብዓት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማስተባበሪያ በማቋቋም በሀገራዊ ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ላይ እየሠራ እንዳለ አስታውሰው የውይይት መድረኩ ወቅታዊና የዩኒቨርሲቲውን ሥራዎች ለማጠናከር አጋዥ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው መሠረቱ የውሃ ሳይንስ እንደመሆኑ ከሀገራችን ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር የተያያዙ የትኩረት መስኮችን አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል፡፡

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ተመራማሪ ዶ/ር ሄኖክ ጌታቸው ‹‹Ethiopia’s Positioning Normative Frameworks of the African Union in Ethiopia’s Foreign Policy for the 21st Century›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ እንዳመላከቱት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላት ሚናና መስተጋብር ከቁሳዊ ባለፈ ከዕሴት፣ ከሰብዓዊ መብትና ከማንነት ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት ባወጣቸው የተለያዩ ሰነዶች የተቀመጡ ስምምነቶችን መተግበርና ዕሴቶችን መከተል፣ ሰብዓዊ መብትን መጠበቅ እንዲሁም መልካም አስተዳደርን ማስፈን ስትችል የተረጋጋች ሆና በቀጠናውም ሆነ በአፍሪካ የተሻለ ሚና እንደምትጫወት ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡ አፍሪካን አስመልክቶ የኢትዮጵያን ስትራቴጂ አንድ ተቋም ብቻውን የማያወጣና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ቅንጅትን የሚጠይቅ በመሆኑ ባለድርሻ አካላቱ በተገኙበት መሰል ጥናታዊ ጽሑፎች መቅረባቸው የተቀናጀ ፖሊሲ ለማውጣት ግብዓት ይሆናልም ብለዋል፡፡

ሌላኛው ጽሑፍ አቅራቢ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ልዑልሠገድ ታደሰ የምንገኝበት ዓለም ዓቀፍ ተለዋዋጭ ሥርዓትና ለኢትዮጵያ ያለው አንድምታ እንዲሁም በተለዋዋጩ ዓለም ውስጥ በስትራቴጂ የመመራት አስፈላጊነትን አስመልክቶ የውይይት መነሻ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

ዓለም ዓቀፉ ሊበራል ሥርዓት በርካታ ጥሩ ጎኖች ያሉት ቢሆንም በአንጻሩ በርካታ ችግሮችን የያዘ መሆኑን ያነሱት አቶ ልዑልሠገድ በልዕለ ኃያላን ሀገራት መካካል ያለው ፉክክርና ውጥረት ዓለም ዓቀፋዊ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሚያስችል ደረጃ መድረሱን ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይህም ለታዳጊ ሀገራት አሉታዊ ተጽዕኖውን ከፍ እንደሚያደርግ ገልጸው ሀገራችን የጀመረችውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የለውጥ መንገዶች ለማስቀጠል ውጫዊ የተመቻቸ ሁኔታን ከመፍጠር አኳያ ጫና ሊያሳድርብን ይችላል ብለዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ የሀገራችንን ዲሞክራሲያዊ እኩልነትና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አጀንዳዎችን ለማጠናከር፣ ከሌሎች ተመሳሳይ የኢኮኖሚ አቅም ካላቸው የአፍሪካ ሀገራት ጋር በመቀናጀት ለመሥራት እንዲሁም አሁን ያለው የዓለም ሥርዓት የታዳጊ ሀገራትን ጥቅም ሊያስጠብቅ በሚያስችል መልኩ እየተለወጠ እንዲሄድና ሁሉም የዓለም ሀገራት ድምጻቸው የሚሰማበትና በጋራ ጉዳዮች ላይ ተወያይተው የጋራ መፍትሄ የሚያመጡበት ዓለም ለመፍጠር የጠራ ስትራቴጂ ያስፈልጋል፡፡ ስትራቴጂው በሀገር አቀፍ ደረጃ ተቀርጾ ሁሉም መሥሪያ ቤቶች በሚተባበሩበትና በተቀናጀ መልኩ ሊተገበር እንደሚገባም በጽሑፋቸው ጠቁመዋል፡፡

በምክክር መድረኩ አምባሳደሮች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ተመራማሪዎችና ከፍተኛ አመራሮች፣ የፌዴራልና የክልል የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ባለድርሻ አካላትና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት