127ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ‹‹ዝክረ ዓድዋ ድል ለብሔራዊ መግባባት›› በሚል መሪ ቃል ያለፈውን ታሪክ በመዘከር፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጸና እና የሀገር ግንባታን በሚያጠናክር መንፈስ የካቲት 23/2015 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር አሕመድ ሀሰን ባስተላለፉት ቁልፍ መልእክት 127ኛው የዓድዋ ድል የጣሊያን ቅኝ አገዛዝ ወረራን ለመከላከል የኢትዮጵያ ሕዝቦች በታሪካዊ አንድነት የተዋጉበትና ድል ያስመዘገቡበት ታሪካዊ ቀን መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን የጣሊያን ቅኝ አገዛዝ መከራንና ወረራን ለመከላከል በአንድነት ባደረጉት ትግል ለመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች በተለይም ለአፍሪካውያን የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግል እንዲያፋፍሙ አበረታችና ፈርቀዳጅ ድል መሆኑን ዶ/ር አሕመድ ገልጸዋል፡፡ የዓድዋ ጦርነት ውጤታማ ይሆን ዘንድ የነበረው ሀገራዊ የመረጃ ፍሰት ዘዴ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የአንድነት፣ የአብሮነትና የመቻቻል ሁኔታ ልዩ አስተዋጽዖ የነበረው በመሆኑ ተሞክሮው እየተፈተሸና እየተቀመረ ለሀገር መልካም ገጽታ ግንባታና ለአሁኑ ትውልድ የሞራል እድገት ወሳኝ ፋይዳ እንዲኖረው ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡

የአሁኑ ትውልድም ድህነትንና ኋላቀርነትን እንዲሁም ሌሎች ወቅታዊ ችግሮችን ለመከላከል የቀደምት አባቶቻችንና አያቶቻችን የኢትዮጵያዊነት ትግልና የድል ልምድ በመቅሰምና ያለሀገራዊ ዝግጅት ጦርነት ገጥሞ ድል መጠበቅ እንደማይቻል ተገንዝቦ ሀገራዊ አንድነትንና ትብብርን በማረጋገጥ ታሪክን ለማስቀጠል የሚያስችል የጋራ አስተሳሰብ መቅረጽ እንደሚገባ ዶ/ር አሕመድ አሳስበዋል፡፡ የዓድዋ ድል በዓለም የአስተሳሰብ ሥርዓት ላይ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣ ድል በመሆኑ በኢትዮጵያ ላይ ወቅቱን እየጠበቀ የሚመዘዝ የቂም በቀል ጦር ሁሌም የሚኖር መሆኑን ጣሊያን ከድሉ ማግስት በተሻለ ዝግጅት ተመልሳ በሀገራችን ላይ የከፈተችው ጦርነት ጥሩ ማሳያ መሆኑን ተገንዝቦ እንደ ታሪካዊት ሀገር ሕዝብና ባለ አደራ ትውልድ አርቆ በማሰብ ከወቅቱ ጋር የሚሄድ ሁሉን አቀፍ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ዶ/ር አሕመድ በአጽንዖት ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን የጥንት አባቶች ጀግንነታቸውንና ለሀገር ያላቸውን ፍቅር ያስመሰከሩበት፣ የሰው ዘር እኩልነትን ያረጋገጡበት፣ ባህል ተጠብቆ እንዲኖር ያስቻሉበት፣ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ ያስከበሩበትና አንድነታቸውን አጉልተው ለዓለም ያሳዩበት ትልቅ ድል በመሆኑ የአሁኑ ትውልድ ብዙ ሊማርበት ይገባል፡፡ ፕሬዝደንቱ አክለውም በአንድነት፣ በመተባበርና በፅናት በመታገል ጠላትን ማሸነፍ የሚቻል መሆኑን ከቀደምት ጀግኖቻችን በወረስነው ወኔና መንፈስ በቆራጥነት በመቆም የሀገርን አንድነት መጠበቅና በድህነት ላይ በመዝመት ለሀገር እድገት መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሙሉጌታ ደበሌ በበኩላቸው ሀገራችን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነፃነታቸውንና ሉዓላዊነታቸውን አስከብረው ከቆዩ ሁለት ሀገራት አንዷ ስትሆን የዓድዋ ድል የካቲት 1888 ዓ/ም ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመቆጣጠር የመጣው የጣልያን ወራሪ ኃይል ድል የተመታበት ነው ብለዋል፡፡ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ድል ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካውያንና በባርነት ቀንበር ሲሰቃዩ ለነበሩ ጥቁር ሕዝቦችና ነፃነት ወዳድ ለሆኑ የዓለም ሕዝቦች ድል ሲሆን ለጥንታዊቷ ኢትዮጵያ መቀጠልና ለዘመናዊ ኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት መወለድ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ዶ/ር ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ት/ክፍል መምህርና ተመራማሪ አቶ ያምራል መኮንን ‹‹የዓድዋ ድል እና ዘመናዊ የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ብሔራዊ ማንነት ግንባታ›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ በዓድዋ ድል የኢትዮጵያን ግዛትና አንድነትን መጠበቅ፣ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ማስከበር፣ ዲፕሎማሲያዊ ዕውቅና ማግኘት እንዲሁም የብሔራዊ አንድነትና ማንነትን መገንባት ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡ መ/ር ያምራል አክለውም የዓድዋ ጦርነት ሁሉም ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት ድል ሲሆን ካህኑ በጸሎት፣ ሴቶች ስንቅ በማቀበል፣ ወኔ በመስጠትና የሕክምና አገልግሎት በማድረግ ቁርጠኝነታቸውን ያሳዩበት ትልቅ ትግል መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የዓድዋ ድል በዓል ላይ መሳተፍ በራሱ ትልቅ ታሪክና ጀግንነት ነው ያሉት የጋሞና ጎፋ ዞኖች ጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ዓለማየሁ በበኩላቸው ጀግኖች አባቶች ዓድዋ ድረስ በመሄድ በከፈሉት መስዋዕትነት የዛሬዋን ኢትዮጵያ ማየት መቻሉን ገልጸው ተተኪው ትውልድ የቀደምት አባቶችን የአርበኝነትና የታሪክ አሻራ በመገንዘብ ለእናት ሀገር አለኝታና ተቆርቋሪ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

የበዓሉ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የዓድዋ ድል ታሪክን ለመጪው ትውልድ በማስተላለፍ በቀጣይ በዓሉን በተሻለ ሁኔታ በአደባባይ በማክበርና ጀግኖች ለሀገራቸው የከፈሉትን መስዋዕትነት በተገቢው ሁኔታ በማወደስ የአሁኑ ትውልድ እንዲነቃቃ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጋባዥ እንግዳ፣ ከጋሞ ዞንና ከአርባ ምንጭ ከተማ ጥሪ የተደረገላቸው የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፣ የጋሞና ጎፋ ዞኖች ጥንታዊት ኢትዮጵያ አባትና እናት አርበኞች፣ የጋሞ አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አመራር አካላት፣ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት