Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ‹‹የምሁራን ሚና ለሀገራዊ መግባባት›› በሚል መሪ ቃል የዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ የሥራ ኃላፊዎችና ተማሪዎች በተገኙበት የካቲት 25/2015 ዓ/ም ውይይት አካሂዷል፡፡ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ምሁራን ሳይንስንና ምርምርን መሠረት ባደረገ መልኩ ለሀገር ሰላም፣ እድገትና ብሔራዊ መግባባት የሚበጁ ጠቃሚ ምክረ ሃሳቦችን ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ዩኒቨርሲቲውም ሆነ በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ ምሁራን በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝደንቱ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የሚደረጉ መሰል የምሁራን ውይይቶችና ክርክሮች ለሀገር ጠቃሚ የሆኑ በርካታ ምክረ ሃሳቦች የሚመነጩባቸው እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ የምሁራን የውይይት መድረኮች ያላቸውን ሀገራዊ ፋይዳ በመገንዘብ ዩኒቨርሲቲው መሰል ውይይቶችን በቋሚነት የሚመራና አጀንዳዎችን የሚቀርጽ አራት አባላት ያሉት ኮሚቴ ማቋቋሙንም ገልጸዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በበኩላቸው እንደ ዩኒቨርሲቲ ከተለመደው ወርክሾፕና ሲምፖዚየም ወጣ ባለ መልኩ በተለያዩ ሀገራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍልስፍናዎች ላይ መነጋገር፣ መወያየትና ብስለትና ጥበብ በተሞላው ሁኔታ የሃሳብ ፍጭት ማድረግ እንደሚገባና በዚህ መልኩ ለቀጣይ ትውልድ ዕውቀትና የውይይት ባህልን ማስተላለፍ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የዚህ ዓይነት የምክክር መድረኮች ካወቁት የምንማርበት፣ ሃሳቦችን አርቀን የምናስብበትና ከችግሮቻችን የምንማማርበት ስለሚሆን በፍጹም ሀገራዊና ምሁራዊ ስሜት መሳተፍ ይኖርብናልም ብለዋል፡፡

በዕለቱ ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ሁለት ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር በሆኑት ዶ/ር ይሄነው ውቡ ‹‹ሀገራዊ ውይይት ለብዝሃነትና የሌሎች ተሞክሮ ለኢትዮጵያ ያለው ፋይዳ›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሑፍ በተለያዩ ሀገራት የተደረጉ የድኅረ ግጭት የሀገር ግንባታ ልምዶች በመነሳት በኢትዮጵያ ሊደረግ ለታሰበው ሀገራዊ ውይይት ብዘሃነትን የማስተናገድ እንዲሁም ጥያቄዎችን የመመለስ ዕድል እንዳለው ለማመላከት ሞክረዋል፡፡ ብዝሃነት ከሀገረ መንግሥት ግንባታ ስኬት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደሌለው የሚገልጹት ዶ/ር ይሄነው እንደ ህንድ ያሉ ከ700 በላይ ማንነት ያለባቸው ሀገራት ብዝሃነት በሀገረ መንግሥት ግንባታቸው ውስጥ ችግር እንዳልሆነ በአንጻሩ ሩዋንዳና ሶማሊያን የመሰሉ ጥቂት ማንነት ያላቸው ሕዝቦች ችግር ውስጥ ሲገቡ መታየቱን ለአብነት አንስተዋል፡፡

የሩዋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቱኒዚያና ሱዳንን የድኅረ ግጭት የሀገር ግንባታ የውይይት ልምዶችን በጽሑፋቸው የዳሰሱት ዶ/ር ይሄነው የተካሄዱት መድረኮች ፍትሕን፣ እውነትና እርቅን ፍለጋ ላይ ያተኮሩ ነበሩ ብለዋል፡፡ ለማሳያነትም በደቡብ አፍሪካ የነበረው የድኅረ ግጭት ውይይት እውነትን ፍለጋና እርቅ ላይ ያተኮረ ሲሆን በአንጻሩ በሩዋንዳ የነበረው ውይይት ፍትሕን ያስቀደመ ነበር ብለዋል፡፡ በመሰል ውይይቶች ላይ ሁሉም አወዛጋቢ ጉዳዮች ለውይይት የሚቀርቡ ሲሆን ሁሉንም ችግሮች በአንዴ መፍታት ስለማይቻል መሠረታዊ ችግሮችን መፍታት ላይ ትኩረት እንደሚደረግም አብራርተዋል፡፡ በብዝሃነት የተፈተኑ ሀገሮች ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠርና ጥያቄዎችን ለመመለስ የሄዱበት መንገድ ተመሳሳይ አይደለም ያሉት ጽሑፍ አቅራቢው በኢትዮጵያ ሊደረግ የታሰበው ብሔራዊ የውይይት መድረክ ከሌሎች ሀገራት ልምድ መቅሰም እንደሚገባው ነገር ግን የሚወሰደው ልምድ የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ ሊሆን እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡

ሌላኛው የውይይት መነሻ ጽሑፍ ‹‹ብዝሃነትና ሕብረ ብሔራዊ ሀገረ መንግሥት ግንባታ በኢትዮጵያ፤ ተግዳሮትና ተስፋ›› በሚል ርዕስ በዩኒቨርሲቲው የሕግ መምህር አቶ ደረጀ ማሞ የቀረበ ሲሆን አቅራቢው በጽሑፋቸው በሀገራዊ ማንነት ግንባታና በሀገረ መንግሥት ግንባታ መካከል ያሉ መስተጋብሮችን፣ በብዘሃነት ውስጥ ሀገራዊ ማንነት ግንባታ ሂደቶችን፣ አሠራሮችንና ማነቆዎችን በስፋት ለመዳሰስ ሞክረዋል፡፡ አቶ ደረጀ በጽሑፋቸው የሀገር ማንነት ግንባታ/Nation Building/ ረዥም ጊዜ የሚወስድና የማያቋርጥ ሂደት ሲሆን ብሔራዊ ማንነትን መገንባት ወይም ማዋቀርን ያካተተና በግዛቱ ውስጥ ባሉ ሕዝቦች መካከል የተረጋጋና ዘላቂነት ያለው አንድነት መኖርን ዓላማ ያደረገ ሲሆን የጋራ መግባባትን መሠረት ያደረገ አካሄድ፣ ፌዴራሊዝምን መተግበር፣ የአናሳ ማኅበረሰብ ክፍሎችን ውክልና ማስተዋወቅና የባህል ነፃነትን ማጠናከር በብዝሃነት ውስጥ ሀገራዊ ማንነትን ለመገንባት የሚጠቅሙ አሠራሮች ናቸው ብለዋል፡፡ እንደ አቶ ደረጃ የሀገረ መንግሥት ግንባታ/State Building/ በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖርን የፍትሕ፣ የደኅንነትና ሌሎች ተቋማት ግንባታን የያዘ ጽንሰ ሃሳብ ሲሆን በሕዝቦች መካከል የሚኖር ስምምነት፣ ሁሉን ያሳተፈ ማኅበራዊ መሰባሰብና ጠንካራ ሀገራዊ ተቋማት ግንባታ መኖር ቅቡልነት ላለው ሀገራዊ ማንነት ግንባታ መኖር ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡

በኢትዮጵያ የሀገራዊ ማንነት ግንባታ ሂደት በርካታ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች ገጥመውታል ያሉት ጽሐፍ አቅራቢው በዋናነት የታሪክ አለመግባባት፣ የዲሞክራሲ ባህል አለመኖር፣ ድህነት፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኢ-ፍትሐዊነት መንሰራፋት፣ የሕገ መንግሥት ቅቡልነት ተግዳሮት፣ የአመራር ክፍተት፣ ክልላዊ/ቀጠናዊ አድሏዊነት፣ የሀገራዊ ተቋማት መድከም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ውስንነት እና የሚዲያዎች የሐሰት ዜናና የጥላቻ ቅስቀሳዎች ዋነኛ ችግሮች ናቸው፡፡ ዘላቂና ለረዥም ጊዜ የሚጸና ሀገራዊ ማንነት ለመገንባት እንደ መከላከያ ሠራዊት ያሉ ጠንካራ ሀገራዊ ተቋማትን የመገንባት እንዲሁም በማኅበረሰቡ መካከል መግባባትን የመፍጠር ጉዳይ ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ያወሱት አቶ ደረጀ የዜጎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ተዘዋውረው የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት ንብረት የማፍራት መብትም ከዚህ አንጻር ሊከበር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በመድረኩ የቀረቡ ጽሑፎችን መነሻ ያደረጉ በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን በቀጣይ መሰል መድረኮች በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ሊዘጋጁ እንደሚገባ አጽንዖት ተሰጥቷል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የተቋቋመው ኮሚቴም የተለያዩ አጀንዳዎችን በመቅረጽ መሰል ውይይቶችን ማሰናዳቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡
                                                                                                                                                                                                                            አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
                                                                                                                                                                                                                               የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
                                                                                                                                                                                                                           የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት