የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ፈጠራ ልማትና ማበልጸጊያ ማእከል ለዩኒቨርሲቲው መደበኛ ተማሪዎች የሥራ ፈጠራ/Entrepreneurship/ ሥልጠና የካቲት 24/2015 ዓ/ም ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ምስሎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የማእከሉ ዳይሬክተር ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔ ሥልጠናው ተማሪዎች ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን ለጎን የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ማፍለቅ እንዲችሉ የሚሰጥ ሲሆን በቀጣይም ማእከሉ በሚያወጣቸው ማስታወቂያዎች መሠረት አዲስ ገቢም ሆኑ ተመራቂ ተማሪዎች ሥልጠናውን መውሰድ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

የማእከሉ ቡድን መሪ አቶ አበበ ዘየደ በበኩላቸው ማእከሉ ለዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችና ለውጭው ማኅበረሰብ ሥልጠናዎችን እንደሚሰጥ ጠቁመው በሥልጠናው የተሳተፉ ተማሪዎች የሥራ ፈጠራ ሃሳቦቻቸውን አቅርበው በሀገር አቀፍ ደረጃ በሥራና ክሂሎት ሚኒስቴር በኩል በሚካሄደው ውድድር እንዲወዳደሩና እንዲሸለሙ የሚረዳቸው ነው ብለዋል፡፡ አክለውም በ2013 ዓ/ም እና 2014 ዓ/ም የዩኒቨርሲቲው ሁለት ተማሪዎች የሥራና ክሂሎት ሚኒስቴር ባዘጋጀው ውድድር ተሳትፈው ከ245 ሺህ - 260ሺህ ብር መሸለማቸውንና በዘንድሮው ዓመትም ብቁ የቢዝነስ ሃሳብ ያቀረቡ ተማሪዎችን ለመላክ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የማኔጅመንት ት/ክፍል መምህርና አሠልጣኝ አቶ ሰብስቤ ሁሴን ሥልጠናው በመሠረታዊ የሥራ ፈጠራ አመለካከትና ክሂሎት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መሰጠቱንና ዓላማውም ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ከተማሩት የትምህርት መስክ ውጭ ተጨማሪ የሥራ ፈጠራ ክሂሎት እንዲኖራቸውና የመንግሥታዊ ሥራ ቅጥር ከመፈለግና የሥራ ማስታወቂያ ከመጠበቅ ይልቅ የራሳቸውን ሥራ ፈጥረው ለራሳቸውና ለሌሎችም እንዲጠቅሙ የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡

የ3 ዓመት የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ተማሪ ቃል ፋንታሁን ሥልጠናውን አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት ሥልጠናው ወደ ራሱ እንዲያይ እንደረዳውና ከዩኒቨርሲቲው ተመርቆ መውጫ ጊዜው ሳይደርስ በመሰጠቱ የራሱን የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ለማመንጨት ዕድል የሚሰጥ መሆኑን ተናግሯል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት