Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ትምህርትና ሥነ ባህርይ ሳይንስ ት/ቤት ለጋሞ ባይራ እና ለአቡነ ሰላማ 2ኛ ደረጃ ሞዴል ት/ቤቶች መምህራንና ተማሪዎች ለመምህራን በሥራ ተነሳሽነት፣ ምዘናና ሥነ ልቦናዊ ዝግጁነት እንዲሁም ለተማሪዎች በጊዜ አጠቃቀም፣ የጓደኛ ግፊት፣ ከዕድሜ ጋር የተያያዙ ለውጦችና የፈተና አወሳሰድ ክሂሎት በመሰሳሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የካቲት 25/2015 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሥነ ትምህርትና ሥነ ባህርይ ሳይንስ ት/ቤት ዲን አቶ አንለይ ብርሃኑ ት/ቤቶቹ ሞዴል ት/ቤቶች እንደመሆናቸው ያላቸውን ሀብትና ጊዜ በአግባቡ ተጠቅመው የተሳካ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲሠሩ የመምህራንንም ሆነ የተማሪዎች አቅም ከመገንባት አንጻር በዕቅድ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡

የት/ቤቱ የማኅበረሰብ ጉድኝት አስተባባሪ ተ/ፕ ዘበነ ተምትም በበኩላቸው ሥልጠናው መምህራን ከዚህ ቀደም የነበራቸውን ዕውቀትና የሥራ ተነሳሽነት ለማነቃቃት የተሰጠ ሲሆን ተማሪዎች በፈተና ጊዜ የሚመጣ ጭንቀትን በመቀነስና የጊዜ አጠቃቀማቸውን ሚዛናዊ በማድረግ ዓላማቸውን እንዲያሳኩ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ አስተባባሪው በማኅበረሰብ ጉድኝት በኩል ለሁሉም ማኅበረሰብ እንደ አስፈላጊነቱ መሰል ሥልጠናዎችን በማዘጋጀት የተሻለ ውጤት ለማምጣት የድርሻቸውን እየሠሩ ነው፡፡

‹‹ጭንቀትን መቆጣጠር›› እና ‹‹ከዕድሜ ጋር የተያያዙ ለውጦችና የአቻ ግፊትን መቆጣጠር›› በሚሉ ርዕሶች ዙሪያ ሥልጠና የሰጡት የሳይኮሎጂ ት/ክፍል መምህር አቶ አዲስዓለም ወልድሻ ተማሪዎች በትምህርት ላይ እያሉ የሚያጋጥማቸውን ውጥረት በዕውቀትና በብልሃት መምራትና ሕይወታቸውን ሊያበላሽ ከሚችል የአቻ ግፊት ተለይተው ወደ ትምህርታቸው ብቻ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው ሰፊ ገለጻ አድርገዋል፡፡

ከሠልጣኝ መምህራን መካከል የጋሞ ባይራ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን የሆኑት ወ/ሮ መታሰቢያ ካሣሁንና አቶ ተሻለ አመለ በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው ራሳቸውን በዕውቀትና በክሂሎት እንዲያጎለብቱ፣ በፈተና ዝግጅት ወቅት በፈተና ይዘቶች ላይ ሊያደርጉ ስለሚገባቸው ጥንቃቄ እንዲሁም ለሥራ ያላቸውን አመለካከት እንዲቀይሩ የረዳቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ወቅቱን የጠበቀ ለውጥ ለማምጣት ያለንን ዕውቀት ማዳበርና በትጋት መሥራት ይጠበቅብናልም ብለዋል፡፡
ሠልጣኝ ተማሪዎች በበኩላቸው ሥልጠናው የአጠናን ዘዴያቸውንና የጊዜ አጠቃቀማቸውን እንዲያሻሽሉ ያገዛቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

                                                                                                                                                                                                                                        አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
                                                                                                                                                                                                                                        የብሩህ ተስፋ ማእከል!
                                                                                                                                                                                                                                     የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት