የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከጋሞ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ጋር በመተባበር በዲታ ወረዳ ዛላ ከተማ ለሚገኙ ወጣት አደረጃጀት አመራርና ለኢንተርፕራይዝ አካላት የአመራርነት እንዲሁም ለቱሪዝም ባለሙያዎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን ማልማትና አስተዳደር ዙሪያ የካቲት 24/2015 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሥራ ፈጠራ አመለካከት፣ ለስኬት የሚያበቁ 10 ዋና ዋና ግላዊ የሥራ ፈጠራ ባህርያት፣ የጊዜ አጠቃቀም፣ የአመራርነት ሚናና ክሂሎት፣ የቢዝነስ ዕቅድ አዘገጃጀት፣ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን ማልማትና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ንጽሕናና ጥራት ማስጠበቅ በሥልጠናው የተዳሰሱ ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው፡፡

የኮሌጁ የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊና አሠልጣኝ መ/ርት አስቴር ሰይፉ እንደገለጹት የሀገርም ሆነ የተቋም ውጤታማነት የሚወሰነው አመራሩ በሚሰጠው ስትራቴጂ በመሆኑ አመራሩን ማብቃት ተቋሙን ብሎም ሀገርን ማብቃት ነው፡፡ አሠልጣኝዋ አክለውም እንደ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ያለው የሥራ መስክና የሥራ ፈላጊው ቁጥር ተመጣጣኝ ባለመሆኑ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መነሻነት ሥራን ከመፈለግ ይልቅ ሥራ ፈጣሪ መሆን ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የራሳቸውን የንግድ ሥራ ለጀመሩ አካላት ሥልጠና የሰጡት የማኔጅመንት ት/ክፍል መምህር አቶ አሰግድ አጥናፉ እንደገለጹት ሥልጠናው በሥራቸው ውጤታማ ሊያደርጓቸው በሚችሉ ባህርያትና አመለካከቶች ላይ ያተኮረ ሲሆን በንግድ ሥራ ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ በርካታ ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ ማለፍና ችግሩን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ውጤታማና ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ በማሳየት የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት የሚረዳ ነው፡፡

የቱሪዝምና ሆቴል ማኔጅመንት ት/ክፍል መምህርና አሠልጣኝ አቶ ፌኔት ሚደቅሳ በበኩላቸው ወረዳውን ለቱሪስት መስህብነት ምቹ ማድረግ፣ ያሉትን የቱሪስት መስህቦች ማስተዳደርና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ንጽሕናና ጥራት ማስጠበቅ ላይ ግንዛቤ ማስጨበጣቸውን ተናግረዋል፡፡ የቱሪዝም ዘርፍ በመንግሥት ሰፊ ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ መሆኑን የጠቀሱት አሠልጣኙ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን ሳቢና ምቹ በማድረግ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ ይቻላል ብለዋል፡፡

የጋሞ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ የወጣቶች ማካተት፣ ንቅናቄና ተሳትፎ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ከተማ ከበደ መምሪያው ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመተባበር በተለያዩ የዞኑ አቅራቢያ ወረዳዎችና ከተሞች ሥልጠና ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰው መሰል ሥልጠናዎችን በማዘጋጀት ወጣቶች ጊዜያቸውን አልባሌ ቦታ ከማዋል እንዲታቀቡና ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን መፍታት እንዲችሉ እንሠራለን ብለዋል፡፡ አቶ ከተማ አክለውም ወጣት አደረጃጀቱ ወጣቶችን ማስተባበር ላይ ትልቅ ኃላፊነት ያለው በመሆኑ ከሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀት በአቅራቢያው ባሉ ቀበሌያት ወርደው ልምድ በማካፈል ወጣቱን ለማብቃት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው እንዲሁም የወረዳው አስተዳደር ድጋፍና ክትትል ሊያደርግ እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የዲታ ወረዳ ም/አስተዳዳሪና የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ መስኮ ከሰላም፣ ከልማትና ከፖለቲካ አንጻር ለሀገር እድገት የወጣቱ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በሥራ አመራር ሂደት፣ ቢዝነስ ፕላን አዘገጃጀትና የወረዳውን ገጽታ ከማስተዋወቅ ጋር በተያያዘ የተሰጠውን ሥልጠና ተግባራዊ በማድረግ ለአካባቢውም ሆነ ለሀገር እድገት ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ሠልጣኞችም በአስተያየታቸው ጥሩ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት የሚረዳ፣ አስተማሪና የሚያንጽ ሥልጠና በመሆኑ በቀጣይ ሰፋ ባለ ጊዜ ቢሰጥ መልካም መሆኑን ተናግረው ለዩኒቨርሲቲውና ላስተባበሩ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

                                                                                                                                                                                                               አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
                                                                                                                                                                                                              የብሩህ ተስፋ ማእከል!
                                                                                                                                                                                                          የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት